የቁርአን የመጀመሪያ ምንጮች

ምዕራፍ አምስት ክፍል አንድ

በቁርአንና በእስልምና ልማድ ውስጥ የዞሮአስተሪያን ተፅዕኖዎች  

REV. W. ST. CLAIR TISDALL, M.A., D.D

ትርጉምና ቅንብር በአዘጋጁ

በተወሰኑ የአረቢያን ባህረሰላጤ አገሮችና በአጎራባቾች ውስጥ ፐርሺያውያን የነበራቸው የፖለቲካ ተፅዕኖ በመሐመድ ጊዜና በፊት በጣም የጎላ እንደነበር ከግሪክና ከአረቢያን ጸሐፊዎች እንማራለን፡፡ ለምሳሌም ያህል አብዱል ፊዳ የነገረን በክርስትያን ዘመን በሰባተኛው መቶ ዓመት መጀመሪያ ላይ ኩስራው (ወይንም አረቦች እንደሚጠሩት ኪስ) አኑሺራቫን ታላቁ የፐርሺያውያን ተዋጊ የሂራ መንግስትን ወረረ፡፡ በውጤቱም በኤፍራጥስ ወንዝ ዙሪያ የነበረውን የሂራ ንጉስን ከዙፋኑ አወረደና በእርሱም ቦታ የራሱን ፍጡር ሙንዲር ማይ ሳማ የተባለውን አስቀመጠ፡፡ ከዚያም ብዙ ሳይቆይ አኑሺራቫን፣ ቫራዝ በሚባል የጦር መሪ ስር ወደ የመን የጦር ሰራዊትን ላከ ይህም አገሪቱን ይገዙ የነበሩትን አቢሲኒያውያንን ለማስወጣትና የመናዊውን ልዑል አቡ ሳይፍን በአባቶቹ ዙፋን ላይ መልሶ ለማስቀመጥ ነበር፡፡ ነገር ግን የፐርሺያውያን ጦር በአገሪቱ ውስጥ ቀረ በመጨረሻም እራሱ የጦር መሪው ወደ ዙፋኑ ወጣና ቆይቶም ለእራሱ ልጆች ዙፋኑን አስተላለፈ፡፡ አቡል ፊዳ የሚነግረን ልዑሉን በሒራ የተኩት የሙንዲር ቤተሰቦች በአረቢያን ኢራቅ ውስጥም ይገዙ ነበር እነርሱም በፐርሺያዊው ንጉስ ስር ገዢዎች ብቻ ነበሩ፡፡ እርሱም የመንን በተመለከተ የተናገረው አራት የአቢሲኒያ ገዢዎችና ስምንት የፐርሺያን ልዑላን የመሐመድን መንግስት ሥልጣን ከመቀበላቸው በፊት ይገዙ ነበረ፡፡ ነገር ግን ከመሐመድ ጊዜ በፊትም እንኳን በፐርሺያውያን ግዛትና በሰሜን ምዕራብ እንዲሁም በምዕራብ አረቢያ መካከል ግንኙነቶች ነበሩ፡፡ እኛም የተነገረን ነገር ኖፋል እና ሙታላብ (የመሐመድ ቅድመ አያት ወንድሞች) የቆራይሽን ጎሳ በገዢነት ይመሩ በነበረበት ጊዜ የመካ ነጋዴዎች ከኢራቅና ከፋርስ (ጥንታዊ ፐርሺያ) ጋር እንዲነግዱ የሚፈቅደውን የሰላም ድርድር ከፐርሺያውያን ጋር አድርገው ነበር፡፡ በ606 ዓመተ ምህረት ወይም በዚያን ገደማ በአቡ ሱፈያን የሚመራ የነጋዴዎች ቡድን ወደ ፐርሺያ ዋና ከተማ ደርሰው በንጉሱ አቀባበል ተደርጎላቸው ነበር፡፡

መሐመድ ለነቢይነቱ ቢሮ ጥያቄውን ባቀረበበት ጊዜ፣ በ612 ዓ.ም ፐርሺያውያኖች ሶርያን፣ ፓለስታይንን እና ኤሽያ ማይነርን ለጊዜው ድል አድርገው ተቆጣጥረው ነበር፡፡ በሂጂራ ወቅት በ622ዓ.ም ደግሞ ንጉሱ ሄራኩለስ የባዛንታይንን ንብረት (ሃብት) ማስመለስ ጀምሮ ነበር፣ ፐርሺያኖች ሰላምን ማድረግ የፈለጉበት ጊዜም ከዚያ ሩቅ አልነበረም፡፡ ከዚህም የተነሳ ባድዛን በየመን የነበረው የፐርሺያው ገዢ ከአገሩ ተስፋ ያደርግ የነበረውን ተስፋ ማግኘት ስላልቻለ ለመሐመድ እጅ መስጠትና ግብር ለመክፈል ተገዶ ነበር (628 ዓ.ም)፡፡ ከነቢዩ ሞት ጥቂት ዓመታት በኋላ የእስላም ጦር ፐርሺያን ድል አደረገና እጅግ በጣም ብዙ የሚሆነውም ሕዝብ በጦር ኃይል ወደ እስልምና እንዲለወጡ አደረገ፡፡

 

አንዱ በጣም በስልጣኔ የገፋና ሌላው በድንቁርና ያሉ ሁለት አገሮች እርስ በእርስ በጣም ተቀራርበው ግንኙነትን ሲፈጥሩ የመጀመሪያው በሁለተኛው ላይ እጅግ በጣም ከፍተኛ የሆነን ተፅዕኖ ያደርጋል፡፡ ታሪክም በሙሉ ይህንን ትምህርት ያስተምረናል፡፡ አሁን በመሐመድ ጊዜ አረቦች በጣም ባልሰለጠነ ሁኔታ ውስጥ ነበሩ በእርግጥ የራሳቸው ጸሐፊ ከእስልምና በፊት የነበረውን ነገር ሲገልፀው እንዲህ ብሏል፡- ‹የድንቁርና ጊዜዎች› ናቸው ብሏል፡፡ ፐርሺያውያን በሌላ ጎኑ ከአቫስታ እንደምንማረው ከዳርየስና ከአርጣክስስ የኩኒፎርም ቅርፃዊ ጽሑፎች ውስጥ አሁንም ካሉት የፐርስፖሊስ ቅሬታዎች ላይ እንዲሁም ከግሪክ ጸሐፊዎች ማስረጃዎች እንደምናገኘው በጣም ሰልጥነው ነበር፤ ቢያንስ በጣም ገና ከጥንት ጊዜ ጀምሮ፡፡ ስለዚህም ከእነርሱ ጋር መገናኘት በአረቦች ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩን ማሰብ ትክክል የሚሆን ነገር ነው፡፡ ከአረቢያን ታሪክ ጸሐፊዎች፣ ከቁርአን አረፍተ ነገሮችና ከተንታኞቻቸው እርግጥ የሆነው ነገር የፍቅር አፈታሪኮችና የፐርሺያውያን ግጥሞች በመሐመድ ጊዜዎች እጅግ በጣም ከፍተኛ የሆነ ዕውቅናን በአረቦች መካከል አግኝተው ነበር፡፡ እነዚህ ተረቶች በቁራይሾች በጣም በስፋት ይታወቁ ነበረ ስለዚህም መሐመድ በጠላቶቹ እነርሱን ወስዶ ወይንም አስመስሎ በቁርአኑ ውስጥ እንዳስቀመጣቸው ይከሰስ ነበር፡፡ ኢብን ሒሻም ለምሳሌ የዘገበው አንድ ቀን መሐመድ፡ ‹ጉባኤን ሰበሰበና፣ ከዚያም በታላቁ እግዚአብሔር ፊት አከማቻቸውና እዚያ ቁርአንን አነበበላቸው፤ እንዲሁም እምነት ሳይኖራቸው ለሚቀሩ አገሮች ምን እንደሚመጣባቸው አስጠነቀቃቸው፡፡ ከዚያም ናድር ቢን አል ሐሪዝ ወደ ስብሰባው የተከተለው ሰው ተነሳና ስለ ጠንካራው ሩስታም እና ስለ ፐርሺያው ንጉስ ኢስፋንዲያር ነገራቸው፡፡ ከዚያም እርሱ እንደዚህ፡- ‹በእግዚአብሔር ይሁንባችሁ! መሐመድ እኮ ከእኔ የተሻለ ታሪክ ነጋሪ አይደለም የእርሱም ንግግር ምንም አይደለም ነገር ግን የጥንቶች ተረት ብቻ ነው እንጂ አላቸው፡፡ ልክ እኔ እንደተናገርኳቸው ነው እርሱም ያቀናበራቸው› አለ፡፡ ስለዚህም በዚህ ንግግር ላይ  እግዚአብሔር የሚከተለውን ጥቅስ አወረደ፡ ‹እነርሱም እንዲህ ብለዋል እርሱ የጥንት ተረቶችን ነው የጻፋቸው እርሱም ጠዋትና ማታ ያስታውሳቸዋል፡፡ አንተ እንዲህ ተናገር በሰማይና በምድር ያለውን ምስጢር የሚያውቀው እርሱ ልኮታል ብለህ ተናገር በእርግጥ እርሱ ይቅር ባይና መሐሪ ነው›፡፡ በእርሱም ዘገባ መሰረት ይህም ደግሞ ከሰማይ የወረደ ነው፡ ‹የእኛ ጥቅሶች በእርሱ በታወሱ ጊዜ እርሱ የተናገረው ነገር የጥንት ተረቶች በማለታቸው ነበር›፡፡ ይህም እራሱ የወረደውም ለእርሱ (ለመሐመድ) ጥቅም ነበር፡- ‹ወዮ ለእናንተ እያንዳንዳችሁ ኃጢአተኛ ውሸታሞች የእግዚአብሔር ጥቅሶች ለእርሱ ሲነበብ የሰማችሁ ከዚያም እርሱ ትዕቢተኛ ሆኖ ቀጠለ ምንም እንዳልሰማቸው በመሆን ስለዚህም ለእርሱ ጥብቅ ቅጣት እንዲሆን የመልካም ወሬ አመጣ›፡፡

 

መሐመድ ለመጣበት ክስ ያመጣው መልስ በአጠቃላይ ለሰሚዎቹ ምላሽ አልሆነም ነበር፡፡ እኛም እንኳን እንዳንጠይቅ አያደርገንም እንዲህ ዓይነት የቁርአን አንቀፆችን መመርመር በቀደሙት ተቃዋሚዎቹ ተደርጎ የነበረውን ጠቀሳ ከመመርመር አያግደንም፡፡

ከዚህ በላይ በናድር የተጠቀሱት ‹የሩስታምና የኢስፋንዲያር እና የፐርሺያ ንጉስ› ያለምንም ጥርጥር ከጥቂት ትውልድ በኋላ  በጣም የተከበረው የፐርሺያ የጀግንነት ገጣሚ ፊርዳውሲ የፐርሺያዊ ገጠሬዎች ከሰሩት ውስጥ ነው ይህንን ትምህርት የተማርኩት በማለት ከነገረን ውስጥ አንዱ ነው እርሱም ፊርዳውሲ በግጥም መልክ በሻሃንሜህ ትቶልናል፡፡ ያለምንም ጥርጥር እነዚህ ሁሉ ተረቶች በሁኔታቸው በጣም ጥንታውያን ናቸው፡፡ ነገር ግን እኛ መጥቀስ ላለብንና ማገናዘብ ላለብን ሁሉ በሻናሜህ ላይ አንመሰረትም፤ ይህም ደግሞ መልካም ነው ምክንያቱም በራሱ በስራው ምንጭነት እንዲሁም በአሁኑ ጊዜ ባለው ግጥማዊ ይዘት ከመሐመድ ጊዜ በኋላ የመጣ ነውና ስለዚህም አጥጋቢ ሆኖ ላይወሰድ ይችላል፡፡ እንዳጋጣሚ ግን በአቫስታና በሌሎች የፓርሲስ ወይንም ዞሮአስተርያን መጽሐፍት ውስጥ ጥንታዊነቱ ምንም ጥያቄ ውስጥ ሊገባ የማይችል ብቁ የሆነ ማስረጃዎች አሉን እኛም የምንጠቁመው ወደ እነዚህ ምንጮች ነው፡፡

የፐርሺያን ንጉስ ተረት አረቦች ሊሰሙት አስደሳች የነበረ መሆኑ ስለዚህም ስለ ሩስታምና ኢስፋነዲያር ሰምተው እንደነበረ፤ በመሆኑም ስለ ጃምሺድ ታሪክም ምንም የማያውቁ አልነበሩም ማለት እንደማይቻል በጥንቃቄ ሊደመደም ይቻል ነበር፡፡ በዞሮአስተር ፊት የአርታ ቪራፍን ወደ ሰማይ መወሰድ በተመለከተ ያለውን የፐርሺያውያንን ተረቶች፣ የእነርሱም የገነት እና የቺነቫት ድልድይ የጡብ ዛፍ ቫፓህ፣ የአሪማን ተረት የመጡት ከጥንታዊ ጨለማ ውስጥ ነው፡፡ እንዲሁም ሌሎችም ብዙዎች አስደናቂ ተረቶች ሙሉ ለሙሉ ለአረቦቹ የማይታወቁ ሆነው ቀርተዋል፡፡ እነርሱ የሚታወቁ ቢሆኑ ኖሮ መሐመድ የክርስትያንና የአይሁድ ተረቶችን እንደተጠቀመባቸው ሁሉ ይጠቀምባቸው ነበር፡፡ ስለዚህም እኛ እንደዚህ ዓይነት የፈጠራ ነገሮች በቁርአንና በሙስሊሞች ልማድ ላይ የጣሉት አንድ ዓይነት ነገር መኖር አለመኖሩን መመርመር ይኖርብናል፡፡ እኛም የምናየው ጉዳዩ ይህ ብቻ እንዳልሆነ ነው ነገር ግን በአንዳንድ ሁኔታዎች እነዚህ የፐርሺያ ተረቶች ያለምንም ጥያቄ የአሪያኖች ናቸው እንጂ በሕንድ ውስጥ በተወሰነ የተለወጠ መልኩ የሚገኙት የሴሜቲክ ምንጭነትም የላቸውም፡፡ በእርግጥ አንዳንዶቹ ለመናገር ያህል ከፊል የሃይማኖቱና ከፊልም ደግሞ የእውቀት ውርስ ናቸው የሁለቱም አገሮች ፐርሺያኖችና ሕንዶች እርስ በእርሳቸው ሲለያዩ እና ጥንታዊ ቤታቸውን ሲለቁ የአርያንሙን ቫይጆ በሄራት አቅራያ ወደ ፐርሺያና ወደ ሕንድ በቅደም ተከተል ፈለሱ ስለዚህም በሁለቱም ሕዝቦች አዕምሮ ውስጥ ተረቶቹም አብረው ሄደዋል፡፡ እንደዚህ ዓይነቶች ሌሎች ሐሳቦች ቆየት ብሎ በፐርሺያ ሳይጀምሩና እንዲሁም በጊዜ ውስጥ ወደ ሕንድ ሳይዛመቱ አልቀሩም፡፡ ስለዚህም በመሐመድ ጆሮ ውስጥ እንደደረሱ እንመለከታለን እንደዚሁም እነርሱ በቁርአንና በልማድ ላይ ያለምንም ተፅዕኖ አልቀሩም፣ በተሰጡት የመሐመድ ተከታዮች ዘንድ እንደተነገረው ሁሉ የሚያፀኑትን ነገር ያገኙት ከእርሱ አንደበት ሰምተው እንደሆነ በማያያዝ ይናገራሉና፡፡

 

1. የሌሊቱ ጉዞ

እዚህ ላይ የምንመለከተው መጀመሪያው ነገር በሙስሊሞች ዘንድ የተከበረውን የመሐመድን የሌሊት ጉዞ ጉዳይ ነው፡፡ ይህም የተጠቀሰው ከአሁን በፊት በጠቀስነው የቁርአን ጥቅስ ውስጥ ነው፡- ‹ያ ባሪያውን ከተከበረው መስጊድ ወደዚያ ዙሪያውን ወደ ባረክነው ወደ ሩቁ መስጊድ በሌሊት ውስጥ ያስኼደው (ጌታ) ጥራት ይገባው ከታምራቶቻችን ልናሳየው (አስኼድነው) እነሆ እርሱ (አላህ) ሰሚው ተመልካቺው ነው› ቁርአን 17.1፡፡

ይህንን ቁጥር በተመለከተ የቁርአን ተንታኞች በምንም መንገድ እንዳልተስማሙ በጣም የታወቀ ጉዳይ ነው፣ አንዳንዶች የሚያስቡት መሐመድ በውስጡ የተጠቀሰውን ጉዞ እንዳደረገ በሕልም አየ በማለት ሲያስቡ ሌሎች ደግሞ ቃል በቃል እንዳለ ወስደውት ከልማድ ብዙ ዝርዝሮችን ጨምረውበታል፡፡ አሁንም ሌሎችም እንደገና በምሳሌያዊና በምትሃታዊ ስሜት ገልፀውታል፡፡ ለምሳሌም ያህል ኢብን ኢሻቅ  የነገረን ነገር ልማዳዊ ስልጣኑን እየሰጠ የመሐመድ ተወዳጅ ሚስት "አይሻ" ‹የእግዚአብሔር ሐዋርያ አካሉ አልጠፋም ነበር ነገር ግን እግዚአብሔር በመንፈስ በዚያን ሌሊት ወደ ጉዞ ወስዶት ነበር› በማለት ትናገር እንደነበረ ነው፡፡ ሌላም ልማድ የዘገበው መሐመድ እራሱ ‹ኣይኔ ተኝቶ ነበር ነገር ግን ልቤ ደግሞ ነቅቶ ነበር በማለት ነው›፡፡ የተከበረው የምትሃታዊው ተንታኝ ሙሂዩድ ዲን ጠቅላላ ዘገባውን በምሳሌያዊ ስሜት ተቀብሎታል፡፡ ይሁን እንጂ እኛ የዚህን የሌሊትን ጉዞ መከሰት ጥያቄ ጉዳይ እዚህ ላይ የምር አድርገን ለመነጋገር አላሰብንም እኛም በዚህ አመለካከት ላይ ብዙ መሄድ አያስፈልገንም፡፡ እጀግ በጣም ብዙ የሚሆኑት የመሐመዳውያን ተንታኞችና ልማዳዊዎች መሐመድ ከመካ ወደ ኢየሩሳሌም እንደሄደ እንዲሁም ደግሞ ሰማይን እንደጎበኘ እንደሚያምኑና ለዚህም እረጅም ዘገባን እንደሰጡ እርግጥ ነው፡፡ ይህም ጉዳይ ማለትም መሐመድ ምን እንዳደረገና ምን እንዳየ በተመለከተ ሙስሊሞች በጥልቅ የሚያዩትና የሚታዘዙት ነገር ነው፡፡ እኛም ነገሮችን ማየት ያለብን ከዚህ ልማድ ጋር ነው፣ ከዚህም በተጨማሪ  የዚህን ልማድ ምንጭ ዋና፣ ዋና ሁኔታዎች ከቀደሙት አፈታሪኮች (ተረቶች) በተለይም ከዞሮአስተሪያን ምንጮች ማግኘት በጣም ቀላል  መሆኑን እናያለን፡፡ ይህም እኛ መሐመድ እራሱ ስለ ሚራጅ ከሰጠው ዘገባ፤ አሁን ለመተርጎም ወደምንሸጋገረው፣ በመነሳት ካመኑት እጅግ በጣም ብዙ መሐመዳውያን ጋር የምናምን ቢሆን የተረቱ አጠቃላይ ፈጠራ የኋለኛው ጊዜ ነው ብለን ብናምንም እንኳን ነገሩ ግን  ይህ እውነት ነው፡፡ በመጀመሪያም የምንጠቅሰው የኢብን ኢሻክን ዘገባ ነው ምክንያቱም በቅድሚያ ያገኘነው እርሱን ነውና፡፡ እርሱም የእርሱ ጽሑፍ ጸሐፊና ከእርሱ ተከታይ በሆነው በኢብን ሒሻም በሚከተለው ሁኔታ ተሰጥቷል፡፡  የተነገረን ገብርኤል መጥቶ መሐመድን ሁለት ጊዜ እንደቀሰቀሰውና ወደ ‹ሌሊት ጉዞ› እንዲሄድ እንደተናገረው ነው ነገር ግን እርሱ እንደገና አንቀላፋ፡፡ ከዚያም እርሱ የቀጠለው፡-

‹በመሆኑም እርሱ (ገብርኤል) ወደ እኔ ለሦስተኛ ጊዜ መጣ ከዚያም እርሱ እኔን በእግሩ ነካኝ እኔም ተነስቼ ተቀመጥሁ፡፡ እርሱም በክንዴ ያዘኝ እኔም ከእርሱ ጋር ቆምኩኝ፡፡ ከዚያም ወደ መስጊዱ በር እርሱ ተላከ እናም እነሆ! ነጭ እንሰሳ (በመልኩ) በአህያና በበቅሎ መካከል የሆነና የፊት እግሩን የሚቆጣጠርበት የኋላውንም እግሩን የሚገዛበት በወገቡ ላይ ሁለት ክንፎች ነበሩት፡፡ እርሱም በሚያይበት መጠን በመሬት ላይ ቁጭ አለ፡፡ በእርሱም ላይ አወጣኝ ከዚያም ከእኔ ጋር ወጣ (በእንደዚህ ዓይነት) እኔን አልቀደመኝም እኔም እርሱን አልቀደምኩትም፡፡ በላዩ ላይ ልወጣ (እንሰሳውን) በተጠጋሁት ጊዜ በኋላው እግሩ ብድግ አለ፡፡ እንደዚሁም ገብርኤል እጁን በጋማው ላይ አደረገ ከዚያም ‹ኦ ብሩክ ነህ አንተ ስለምትሰራው አታፍርም (በእግዚአብሔር እምላለሁ) ኦ ብሩክ፣ ከእግዚአብሔር ባሪያ ከመሐመድ በስተቀር ማንም ከዚህ በፊት ተቀምጦብህ አያውቅም ከእርሱም በላይ በእግዚአብሔር ዘንድ በጣም የተከበረ ማንም የለም፡፡ ከዚህም በኋላ ቡራክ በጣም አፈረና ላብ አላበው፡፡ ከዚያም እኔ እስከምቀመጥበት ጊዜ ቀጥ ብሎ ቆመ›፡፡ ‹አል ሐሳን በልማዱ ውስጥ የተናገረው የእግዚአብሔር ሐዋርያ ሄደ እንዲሁም በቅዱሱ ቤት በኢየሩሳሌም እስኪደርስ ድረስ ገብርኤል ከእርሱ ጋር ሄደ፡፡ እዚያም አብርሃምን ሙሴንና ኢየሱስን ከነቢያት ቡድን መካከል ሆነው አገኛቸው፡፡ ከዚያም የእግዚአብሔር ሐዋርያ የእነርሱ የአምልኮ መሪ (ኢማም) ሆኖ መታየት ጀመረ፣ ከእነርሱም ጋር ፀለየ ከዚያም ገብርኤል ሁለት ፅዋዎችን አመጣ በአንደኛውም ውስጥ ወይን ጠጅ በሌላው ደግሞ ወተት ነበረበት፡፡ በመሆኑም የእግዚአብሔር ሐዋርያ የወተቱን ፅዋ ወስዶ ጠጣና የወይን ጠጁን ፅዋ ተወው፡፡ ስለዚህም ገብርኤል እንዲህ አለው ‹አንተ ወደ ተፈጥሮ ነው የተመራሃው የአንተም ሕዝቦች ወደ ተፈጥሮ ይመራሉ፣ ኦ መሐመድ ወይን ለአንተ የተከለከለ ነው፡› ከዚያም የእግዚአብሔር ሐዋርያ ከዚያ ወጣ ጠዋትም በሆነ ጊዜ እርሱ ወደ ቋራይሽ ሄደ ይህንንም መረጃ ነገራቸው፡፡ ከዚያም ብዙ ሰዎች እንደዚህ፡ ‹በእግዚአብሔር! ይህ ነገር ግልፅ ነው በእግዚአብሔር! ከመካ ወደ ሶርያ ለመሄድ ለተጓዦች አንድ ወር ይፈጅባቸዋል ለመመለስም ደግሞ ሌላ ወርን ይወስድባቸዋል ያ ሰው መሐመድ በአንድ ሌሊት ውስጥ ሄዶ ወደ መካ ተመለሰን?› አሉ፡፡

በዚህ ትረካ መሰረት መሐመድ ከመካ ወደ ኢየሩሳሌም የሄደውና የተመለሰው በአንድ ሌሊት ነው፡፡ የኋላ ልማዶች ሁሉም ጉዞውን በጣም አጉልተውታል፡፡  ይሁን እንጂ ትረካው የመጣው አስታዋሹ ከተናገረው ከመሐመድ ከእራሱ ነው በማለት ነው፡፡ በሚሽካቱል ማሳቢ የሚከተለው ትረካ ተሰጥቷል ይህም ከተለመደው ልማዶች ከተላለፈባቸው የስሞች ክትትል ጋር ተያይዞ ነው፡-

‹የእግዚአብሔር ነቢይ ያያያዘው፡ ተኝቼ እንደነበረ እነሆ ተከታዩ (መጪው) ወደ እኔ መጣ፣ ከዚያም እርሱ በዚህና በዚያ መካከል ያለውን ከፈተው ደግሞም ልቤን አውጥቶ ወሰደው፡፡ ከዚያም እምነት የሞላበት ወርቃዊ ፅዋ መጣልኝ፡፡ ልቤም ታጥቦ ነበር እናም ተተካ ከዚያም ወደ እራሴ ተመለስኩኝ ከዚያም እንሰሳ መጣልኝ እርሱም ከበቅሎ አነስ ያለ ከአህያ ደግሞ ከፍ ያለ ነበር፡፡ ነጭም ነበር እርሱም ቡራክ በመባል ተጠራ እርሱም የፊት እግሩን ከሚያየው አርቆ ዘርግቶት ነበር፡፡ ከዚያም እኔ በእርሱ ላይ ተቀመጥሁ ገብርኤልም እስከ ዝቅተኛው ሰማይ እስክደርስ ድረስ ተሸከመኝ፡፡ እርሱም የመግቢያ ፈቃድን ጠየቀ፡፡ እንዲህም ተብሎ ነበር፡- ‹እርሱ ማነው?› እርሱም አለ፡ ‹ገብርኤል› ነው ተባለ፡፡ ‹ደግሞም ከአንተ ጋር ያለው ማነው?› እርሱም አለ ‹መሐመድ ነው› ከዚያም ተባለ፡ ‹እርሱ ተልኮ ነበርን?› እርሱም አለ፡ ‹አዎን› ከዚያም እንዲህ ተብሎ ነበር፡- ‹እንኳን ደህና መጣ የእርሱ መምጣት በጣም ጥሩ ነው› ከዚያም አንዱ ከፈተው እንደገባሁም እነሆ አዳም በዚያ ነበረ፡፡ ገብርኤልም አለ፡ ‹ይህ አባትህ አዳም ነው ስለዚህም ሰላምታ ስጠው› እኔም ሰላምታን ሰጠሁት እርሱም ሰላምታዬን መለሰልኝ፡፡ ከዚያም እርሱ እንዲህ አለ፡- ‹ለጥሩው ልጅና ለጥሩው ነቢይ አቀባበል›፣ ታሪኩ ከአሰልቺውና በጣም ተመሳሳይ ድግግሞሹ ጋር ይቀጥላል፡፡ ገብርኤል መሐመድን ከአንድ መንግስተ ሰማይ ወደ ሌላ መንግስተ ሰማይ እንደወሰደው እየነገረን በእያንዳንዱ በር ላይ ተመሳሳይ ጥያቄን እየተጠየቀ እንዲሁም በትክክል አንድ ዓይነት በሆነ መንገድ መልስን እየሰጠ ነው፡፡ በሁለተኛው ሰማይ ላይ መሐመድ ከመጥምቁ ዮሐንስና ከኢየሱስ ጋር እንዲተዋወቅ ተደርጓል፣ በሦስተኛው ደግሞ ከዮሴፍ ጋር በአራተኛው ከኢድሪስ በአምስተኛው ከአሮን በስድስተኛው ደግሞ ከሙሴ ጋር እንዲተዋወቅ ተደርጓል፡፡ የኋለኛውም አለቀሰ፣ ለምን እንዳለቀሰ ሲጠየቅም እርሱም የመለሰው ያለቀሰበት ምክንያት ከእርሱ ተከታዮች ይልቅ የመሐመድ ተከታዮች መንግስተ ሰማያት ስለሚገቡ እንደሆነ መለሰ፡፡ በሰባተኛው ሰማይ ውስጥ መሐመድ አብርሃምን አገኘው ከዚያም የተለመደው ሰላምታ ተካሄደ፡፡ ‹ከዚያም በኋላ ወደ ስድራቱል ሙንታሃ ወደ ላይ ተወሰድሁ እነሆም ፍሬዎቹ እንደ ሸክላ ሰራተኛ ገምቦዎች ነበሩ እንዲሁም እነሆ ቅጠሎቹ ልክ እንደ ዝሆን ጆሮዎች ነበሩ፡፡ እርሱም አለኝ፡ ‹ይህ የድንበሩ ቅዱስ አበባ ዛፍ ነው› ከዚያም እነሆ አራት ወንዞች ሁለት የውስጥ ወንዞች እንዲሁም ሁለት የውጭ ወንዞች ነበሩ፡፡ እኔም አልኩኝ ‹እነዚህ ሁለቱ ምንድናቸው ኦ ገብርኤል?› እርሱም አለኝ፡ ‹ሁለቱ የውስጦቹ ወንዞች በገነት ውስጥ ናቸው ነገር ግን ሁለቱ የውጭዎቹ አባይና ኤፍራጢስ ናቸው›፡፡

ክፍሉ የጉዞውን ብዙ ሌሎች ጥቃቅኖች ነገሮችን በመዘርዘር ይቀጥላል፣ ከሌሎቹም ክስተቶች መካከል የጠቀስነው የአዳም ለቅሶ ክስተትና እዚህ ሁሉንም ለመጥቀስ አስፈላጊ ያልሆኑት ይገኙበታል፡፡

በታወቁት ስራዎች ውስጥ እጅግ በጣም ብዙዎቹ ዘመናዊ ሙስሞሊች የነቢያቸውን ሕይወት በተመለከተ እውቀት ካገኙባቸው የሚራጅ ዘገባ እጅግ በጣም ብዙ አስደናቂ ነገሮችን የተሞላ ነው፡፡ በውቦቹ አበቦች ድንበር ላይ በደረስን ጊዜ ገብርኤል ከዚያ በኋላ  ከእርሱ ጋር ለመሄድ አልደፈረም ስለዚህም ኢስራፊል የሚባለው መልአክ መሐመድን በሃላፊነት ተረክቦ በግዛቱ ውስጥ መራው፣ እዚያም ነቢዩ እስከ እግዚአብሔር ዙፋን ድረስ ገሰገሰ በእግዚአብሔር በራሱ ድምፅም ጫማውን እንዳያወልቅ ተነግሮት ነበር፣ ምክንያቱም የእነርሱ መንካት የእግዚአብሔርን አደባባይ ሊያከብሩት ስሊሚችሉ ነበር፡፡ ከጥቂት ተጨማሪ ዝርዝሮች ቀጥሎም፣ ማለትም ለተራ እንኳን አዕምሮ ሕፃናዊ፤ ደረቅና ስድበ እግዚአብሔራዊ ከሆኑት፣ በተጨማሪ የተነገረን መሐመድ የገባው ከመጋረጃው በስተጀርባ እንደነበረ ነው እናም እግዚአብሔር ለእርሱ እንዲህ ‹ሰላም ለአንተ ይሁን የእግዚአብሔርም ምህረት የእርሱም በረከት ኦ ነቢዩ!› አለው፡፡ በእነዚህ የሚራጅ የኋለኞች ትረካዎች ውስጥ የምናገኘው የፈጠራ ተረትን ሲሆን በውስጡም ለእውነትና ወይንም ለጤነኛ ምክንያታዊ ሐሳብ ምንም ማዕቀብ ሳይደረግበት ነው፡፡

አሁን እኛ መጠየቅ ያለብን የዚህ የመሐመድ የሌሊት ጉዞ ሐሳብ የመጣበት የመጀመሪያው ምንጭ ምን ነበር? የሚለውን ነው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ይህ አፈታሪክ ከመሐመድ ጋር የተያያዘው በሕልም ላይ ተመሰርቶ የነበረ መሆኑ በጣም የሚቻል ሲሆን ወደ ሰማይ የማረግ ሐሳብ ግን በፍፁም ያልነበረው ይመስላል፤ ይህም ቁርአን 53.13-18 የኋለኛው ቀናት እንደሆነ አድርገን ብንመለከት ነው፡፡ ነገር ግን በልማድ ውስጥ ካሉት ታሪኮች ጋር ማየት ይኖብናል እነዚህም ስለሚራጅ ወይንም መውጣት (ማረግ) በጣም ጥብቅ የሆኑ ዝርዝሮችን ይዘዋል›፡፡ ይህ ተረት በዚህ መልክ የተፈጠረው በዚህ በኩል በሌሎቹ ሁሉ እንደሆነው ሁሉ መሐመድ ከማንኛውም ዓይነት ነቢይ እጅግ በጣም ዕድል የተሰጠው (የተከበረ) መሆኑን ለማሳየት እንደሆነ ለማመን የሚያስችል መልካም ምክንያትን እናገኛለን፡፡ ታሪኩም ብዙ ነገሮችን ከብዙ ቦታዎች ሁሉ ያጠራቀመ ነው ነገር ግን በአርታ ቪራፍ የማረግ ታሪክ ዘገባ ላይ በዋነኛነት የተመሰረተ ይመስላል፡፡ ይህም የሚገኘው በፓላቪ መጽሐፍ ላይ ነው የሚታወቀውም ‹የአርታ ቪራፍ መጽሐፍ› ተብሎ ነበር፣ እርሱም የተጠናቀረው በአርዳሽር ባብጋን የፐርሺያ ንጉስ ጊዜያት፤ ከመሐመድ ሂጂራ 400 ዓመታት በፊት ነበር፣ ይህም የዞሮአስተሪያንን ዘገባዎች ካመንን ነው፡፡

በዚያ ስራ ላይ የተነገረን ነገር በፐርሺያን ግዛት የዞሮአስተሪያንን እምነት በከፍተኛ ደረጃ ከሕዝቡ አዕምሮ ውስጥ ያለውን ቦታ ቀስ በቀስ ጥሎ እንደነበር በማወቅ የማጂያን ቀሳውስት በአዲስ ማስረጃ እምነቱን እንደገና ለማደስና ለመደገፍ ቆርጠው  ነበር፡፡ ይህም የአርዳሸር ቅናት ለማከናወን የጀመረው ነበር፡፡ ስለዚህም የቅዱስነት ሕይወት የሚመራ ወጣት ካህንን መረጡ እናም በተለያዩ የማንፃት ስርዓቶች ወደ ሰማያት ሄዶ በሰማይ የነበረው ነገር ምን እንደሆነ እንዲመለከት፤ በእነርሱ የሃይማኖት መጽሐፍት ውስጥ ካለው ጋር የሚስማማ መሆኑንና አለመሆኑን ተመልሶ እንዲናገር ነበር፡፡ ይህ ወጣት ወንድ ሰው አርታ ቪራፍ ከአዕምሮው ውጪ (በራዕይ ውስጥ) በነበረበት ጊዜ መንፈሱ በመላእክት አለቃ በሳሮሽ መሪነት ወደ ሰማያት አረገ፣ ከዚያም ከአንድ ሕንፃ ወደሌላው ተላለፈ ቀስ በቀስ  በራሱ ‹በአርማዝድ› ፊት እስከሚቀርብ ድረስ፡፡ አርታ ቪራፍ ሁሉን ነገር በሰማያት ባየ ጊዜ እንዲሁም የነዋሪዎቹን ደስተኛ ሁኔታ ኦርማዝድ እንደ እራሱ መልእክተኛ ሆኖ ወደ ምድር እንዲመለስና ለዞሮአስተራውያን ያየውን ነገር እንዲናገር አዘዘው፡፡ ይህንንም እንዳለ መጥቀስ አስፈላጊ አይደለም ነገር ግን ጥቂት ጥቅሶችን መጥቀስ ይህ እንደ ሞዴል ማስረጃነት ለመሐመድ ወደ ሰማይ ማረግ የመሐመዳን ተረት ሞዴልነት እንዴት እንዳገለገሉ ለማሳየት ይጠቅማል፡፡

በአርታ ቪራፍ ናማክ (ምዕራፍ 7 ቁጥር 1-4) ላይ የምናነበው ‹እኔም በከዋክብት ፎቅ ላይ በሁማት ውስጥ አንድ እርምጃ ወደ ፊት ተራመድሁ እኔም የእነዚያን የቅዱሳንን ነፍሳት አየሁኝ ከእነርሱም ፀሐይ ልክ እንደ ብሩህ ኮከብ ይሰራጫል፡፡ እዚያም ዙፋንና መቀመጫ ይገኛል እርሱም በጣም ብሩህ ከፍ ያለና የከበረ ነው፡፡ ከዚያም እኔ ስለ ቅዱስ ሳሮሽ ጠየቅሁኝ፣ ከዚያም አዳር ለሚባለው መልአክ ‹ይህ ቦታ ምንድነው እነዚህስ ሰዎች እነማናቸው?› አልኩኝ፡፡

ይህን አንቀፅ በማብራራት በኩል ‹የከዋክብት ፎቅ› የተባለው የመጀመሪያው ወይንም ዝቅተኛው የዞሮአስተሪያን ገነት አዳር መልአኩ በእሳት ላይ የሚገዛው አደባባይ መሆኑ መገለጥ አለበት፡፡ ሳሮሽ የመታዘዝ መልአክ ነው እርሱም ‹ዘላለማዊ ቅዱስ የሆነው› አንዱ ነው (አመሻ ስፔንታስ በኋላ አምሻስፓንዳስ) ወይንም የዞሮአስተሪያን እምነት የመላእክት አለቃ፡፡ እርሱም ልክ ገብርኤል ለመሐመድ እንዳደረገው አርታ ቪራፍን በተለያዩ ሰማያት ውስጥ መርቶታል ፡፡

ትረካው አርታ ቪራፍ እንዴት ወደ ጨረቃ ፎቅ እንደደረሰ በመናገር ይቀጥላል ወይንም ሁለተኛው እናም የፀሐይ ፎቅ ሦስተኛው የሰማያዊ መኖሪያ ቦታዎች ውስጥ፡፡ በተመሳሳይ መንገድ እርሱ በእያንዳንዱ ሰማይ ውስጥ ተጉዟል በኦርማዝድ መኖሪያ ደርሶ ከእርሱ ጋር እስኪተዋወቅ ድረስ እናም በምዕራፍ 11 ውስጥ እንደሚከተለው የተገለፀውን ቃለ መጠየቅ እስከሚያደርግ ድረስ፡-

‹እናም በመጨረሻ ከዙፋኑ ላይ ተነሳ ወርቅ ተደርቦበት የመላእከቱ አለቃ ባህማን፡ እርሱም እጄን ይዞ ወደ ሁማትና ሁካት እና ሁራስት አመጣኝ በኡርማዝድና በመላእክቱ አለቃ መካከል እንዲሁም ሌሎቹ ቅዱሳን እና የዞሮአስተር ቅዱስ አዕምሮ እንዲሁም ሌሎቹ የታመኑት እና የእምነት አለቃዎቹ ከእዚህ በፊት እንደዚህ ብሩህ የሆነ እና የተሻለ አይቼ አላውቅም ነበር፡፡ ከዚያም ባህማን (አለ) ‹ይህ ኦርማዝድ ነው› እኔም በእርሱ ፊት ሰላምታን ለማቅረብ ወደድሁ፡፡ እርሱም አለኝ ‹ሰላምታ ላንተ ይሁን ኦ አርታ ቪራፍ! እንኳን ደህና መጣህ አንተ የመጣኸው ከሚጠፋው ዓለም ወደዚህ ወደማይበከለው ብሩህ ቦታ ነው› ከዚያም እርሱ ቅዱስ ሶራሽንና አዳር መልአኩን አዘዛቸው፡፡ ‹አርታ ቪራፍን ተሸከሙት ዙፋኑንና የቅዱሳንን ሽልማት አሳዩት እንዲሁም ደግሞ የክፉዎችን ቅጣት› በመጨረሻም ቅዱስ ሳሮሽ እና መልአኩ አዳር እጄን ያዙ እኔም በእነርሱ ከቦታ ቦታ ተወሰድሁ እኔም የመላእክት አለቆችንና ሌሎችንም መላእክትን አየሁኝ›፡፡

ከዚያም የተነገረን ነገር በጣም በዝርዝር አርታ ቪራፍ እንዴት ገነትንና ሲዖልን እንደጎበኘና በእያንዳንዳቸውም ውስጥ ምን እንዳየ ነው፡፡ ሲኦልን ከጎበኘ በኋላ ትረካው ይቀጥላል፡-

‹በመጨረሻም ቅዱስ ሳሮሽና መልአኩ አዳር እጄን ይዘው ከጨለማው ውስጥ አወጡኝ አስፈሪና አስፀያፊ ቦታ ነው፣ እንዲሁም ወደ ብርሃኑ ቦታ የኦርማዝድና የመላእክቱ አለቃዎች ወደተሰበሰቡበት ቦታ ወሰዱኝ፡፡ ከዚያም በኦርማዝድ ፊት ሰላምታን ለማቅረብ ተመኘሁ፡፡ እርሱም ደግ ነበር፡፡ እርሱም አለ ‹ኦ ታማኙ አገልጋይ ቅዱስ አርታ ቪራፍ የኦርማዝድ አምላኪዎች ሐዋርያ አሁን ወደ ተጨባጩ ዓለም ሂድ እኔ ኦርማዝድ እዚህ ማን እንደሆንሁ ልክ እንዳየኸውና እንዳወቅኸው እውነትን ለፍጥረታት ሁሉ ተናገር፡፡ እውነትንና በትክክል የሚናገር ማንም ቢኖር እኔ እሰማዋለሁ አውቃለሁም፡፡ ለጥበበኞች ተናገር› ኦርማዝድ እንዲህ ሲናገር እኔ ተደንቄ ቀረሁ ምክንያቱም ብርሃንን አየሁኝ እንጂ አካልን አላየሁምና እኔም ድምፅን ሰማሁኝ እኔም ‹ይህ ኦርማዝድ እንደሆነ አወቅሁ›፡፡

በመሐመዳን የመሐመድ ሚራጅና በዚህ ትረካ መካከል እጅግ በጣም መመሳሰል ያለ መሆኑን መጥቀስ አስፈላጊ አይደለም፡፡

 

በዛርዱሽት ናማህ ውስጥ ምናልባትም በአስራ ሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በተቀናበረ ስራ ውስጥ በክርስትያኖች ዘመን ዞሮአስተር እራሱ የተያያዘበት ተረት አለ ይህም ከአርታ ቪራፍ አንድ ሺ ዓመት የሆነ ሲሆን እርሱም ወደ ሰማይ እንደወጣና ሲዖልንም ለመጎብኘት ፈቃድን እንዳገኘ ነው፡፡ እዚያም የተነገረን እርሱ አሂራምን እንዳየ ነው ይህም እራሱ ከቁርአኑ ኢብሊስ ጋር በጣም የተቀራረበ ነው፡፡

እነዚህ አፈታሪኮች ለፐርሺያውያን የአርያን ዓለም ክፍል ላይ ብቻ የተወሰኑ አይደሉም፡፡ በሳንስክሪት ውስጥ እኛ ተመሳሳይ ተረት አለን ከእነርሱም መካከል ኢንድራሎካጋማናም ወይንም ‹ወደ ኢንድራ ዓለም ጉዞ› የከባቢው አየር አምላክ ጉዞ አለበት፡፡ እዚያም እኛ የተነገረን ነገር ጀግናው አርጁና በሰማያት ውስጥ ጉዞን እንዳደረገ ነው፡፡ የኢንድራን ሰማያዊ ቤተመንግስት ወዳየበት ቦታ ቬቫንቲ በተባለውና ናንዳናም በተባለው የአትክልት ቦታ ላይ በቆመው፡፡ ሂንዱ መጽሐፍ የሚነግረን ሁሌ የሚመነጨው ውሃ አዲስ አረንጓዴ የሆኑትንና በዚያ ቦታ ውብ በሆነ ቦታ የሚበቅሉትን እንዲሁም በእርሱ መካከል ፓክሻጃቲ የሚባል ዛፍ ቆሟል እርሱም አሚታን የመሰለ ወይንም የአለመሞትን ፍሬዎችና ያፈራል፣ ይህም በግሪክ ገጣሚዎች አምብሮስያ የተባለው ሲሆን ማንም ከእርሱም ቢበላ አይሞትም፡፡ በጣም የሚያምሩ የተለያዩ ቀለማት ያለቸው አበቦች ዛፉን አስጊጠውታል እናም ማንም በጥላው ውስጥ ቢያርፍ በልቡ ያሰበውን ወይንም የተመኘውን ማንኛውንም ነገር ይሰጠዋል፡፡ ዞሮ አስተሪያንስም እራሳቸው የአስደናቂ ዛፍ መኖር ዘገባ አላቸው፡፡ የዛፉም ስም  ‹በአቨስታ ቫፓ› ሲሆን በፓላቪ ደግ ሁማያ ነው፣ በሁሉም በኩል ትርጉሙ ‹መልካም ውሃ ያለው› እና ‹በሚገባ ውሃ የጠጣ› ማለት ነው፡፡ በቪንዲዳ ደግሞ በሚከተሉት ቃላት ተገልጧል፡- በንፅህና ውሃዎች ይፈሳሉ ከፑቲካ ባህር ወደ ቮረካሻ ባህር ውስጥ ወደ ቫፓ ዛፍ፡ እዚያም ሁሉም ዓይነት ዛፎች ያድጋሉ› ቫፓ እና ፓካሽጃቲ ከቱባ ጋር ተመሳሳይ ናቸው› ወይንም ‹የመልካምነት ዛፍ› በመሐመዳውያን ገነት ውስጥ ይህም እዚህ ላይ በጣም ገለጣ የሚያስፈልገው ነው፡፡

ይሁን እንጂ መታወቅ ያለበት ነገር በጣም ተመሳሳይ የሆኑ ተረቶች በአንዳንድ ክርስትያን አፖክሪፋል ስራዎች ውስጥ የሚገኙ መሆናቸው ነው፡፡ በተለይም ደግሞ በ ‹ቪዥዮ ፖሊ› ማለትም ‹በጳውሎስ ራዕይ› እና ‹የአብሃም ኪዳን› ላይ ይገኛሉ፡፡ የኋለኛውን ከዚህ በፊት ከአንድ ጊዜ በላይ ጠቅሰነዋል፡፡ ‹በጳውሎስ ራዕይ› ውስጥ የተነገረን ነገር ጳውሎስ ወደሰማይ እንደሄደና አራቱን የገነትን ወንዞች እንዳየ እንዲሁም አብርሃም በተረቱ ውስጥ የሰማይን አስደናቂነት እንደገለጠ ነው፤ ሁለቱም ወደ መሬት ተመልሰው ያዩትን ለመናገር ተመልሰዋል፣ ይህም ልክ እንደ አርታ ቪራፍ እና መሐመድም አድርገውታል እንደተባለው ነው፡፡ ስለ አብርም የተባለው ነገር ‹የመላእክት አለቃው ሚካኤል ወረደና አብርሃምን በኩሪቤል ሰረገላ ላይ ይዞት ወጣ እንዲሁም እርሱን ወደ ሰማይ ነፋስ ውስጥ ወሰደው እርሱንና ሌሎች ስድሳ መላእክትን  ወደ ደመናው ላይ አመጣቸው፣ አብርሃምም በሰው በተያዘ ምድር ሁሉ ላይ በማመላለሻ ላይ ሆኖ ይጓዝ ነበር›፡፡

ይህ የ‹ኩሪቤል ሰረገላ› የሚመስለው የሌላ መሐመዳውያን አፈታሪክን ነው፣ ምክንያቱም መሐመድ ቡራክ የተባለን እንሰሳ ይጋልብ ነበርና፣ መጋለብ በአረቢያን ሐሳብ ከመንዳት የበለጠ ትርጓሜ አለው፡፡ ቡራክ የሚለው ቃል ከዕብራይስጥ ባራክ ‹መብረቅ› በአረብኛ ደግሞ ‹ባርቅ› ከሚለው የመጣ ሳይሆን አይቀርም ምንም እንኳን የፓለቪ አመጣጥ የሚቻል ቢሆንም፡፡

ሌሎች ነጥቦችን ለመመልከት ከመሄዳችን በፊት የሄኖክ መጽሐፍ እጅግ ረጅም የሆነ የምድርን ድንቅ ነገር የያዘ ረጅም ዘገባ እንዳለው መረዳት አስፈላጊ ነው ሲዖልና ሰማይ ሄኖክ በራዕዩ ያየው፡፡ የዚህ የአፖክሪፋል ስራ በ‹ጳውሎስ ራዕይ› ውስጥ እና ‹በአብርሃም ኪዳን› እንዲሁም በውጤቱ በመሐመዳን ትረት ውስጥ ትልቅ ተፅዕኖ እንዳላቸው ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ነገር ግን እኛ የአርታ ቪራፍ ናማክ በዚህ ተነክቶ የነበረ መሆኑን በጭራሽ መገመት አንችልም፡፡ ምናልባትም በተዘዋዋሪ በእነዚህ ስራዎች ካልሆነ በስተቀር፡፡ ይሁን እንጂ ያ የአሁኑን የእኛን ምርምር የሚነካ ጉዳይ አይደለም፡፡

በኤድን ገነት ውስጥ የነበረውን የሕይወት ዛፍን በተመለከተ አይሁዶች እጅግ ብዙ የሚሆኑ አስደናቂ አፈታሪኮች አሏቸው ይህም ምናልባት ከአካድያን ተረት የተዋሱት ሳይሆን አይቀርም ‹የኢሪቱ ቅዱስ ዛፍ› ይህም በ ዶ/ር ሂልፐርችት ምርመራ አማካኝነት የተጠቀሰው በኒፑር ከተገኘው ከአንዳንድ የጥንት የቅርፅ ጽሑፎች ላይ ነው፡፡ በእነዚህም ውስጥ እኛ በጣም በጥልቅ መግባት አይኖርብንም ነገር ግን በቀላሉ ማድረግ ያለብን  በእነዚህ ተረቶች እና በዘፍጥረት ታሪክ መካከል ምን ያህል ታላቅ የሆነ መነፃፀር መኖሩን በቀላሉ ለመመልከት እንችላለን፡፡ አይሁዳዊው አፈታሪክ የመሐመዳውያንን ሰማያዊ ገነት ዘገባ በጣም ነክቶታል፣ ምክንያቱም ሙስሊሞች የሚያምኑት የኤድን ገነት የሚገኘው በሰማይ ነው በማለት ነውና፡፡ ስለዚህም አይሁዶች ለምድራዊ ገነት የተናገሩትን ሁሉ መሐመዳውያን ደግሞ ለሰማያዊዋ ገነት አስተላልፈውታል፡፡ በዚህም በኩል በአፖክሪፋዊ መጽሐፍት ሳይሳሳቱ አልቀሩም፣ ለአራቱ ወንዞች ገለጣ እንዲሁም ወ.ዘ.ተ፡፡ በ‹ጳውሎስ ራዕይ› ውስጥ  (ምዕራፍ 45) ለተሰጠው፤ በመሠረቱ ሁሉም የመነጩት ከተመሳሳዩ እንግዳ ምኞት ነው፡፡ እነዚህ የአፖክሪፋዊ መጸሐፍት በማንኛውም የክርስትያን ቤተክርስትያን ክፍል እንደ ስልጣን መጽሐፍት ክብደትና ተቀባይነት በፍፁም ያልነበራቸው እንደነበረ መናገር በጣም አስፈላጊ አይደለም፣ ምንም እንኳን አንዳንዶቹ በአንድ ወቅት ባልተማሩት በብዙዎቹ ዘንድ እጅግ በጣም ታዋቂነት የነበራቸው ቢሆንም፡፡ መሐመዳውያን የቱባ ዛፍ ዘገባቸውን ከዞሮአስተርያውያን ወይንም ከአይሁዶች ተረት ቢያመጡትም፣ ወይንም ሁለቱም ኋለኞቹ (አንድ ዓይነት ምንጭ ኖሯቸው) በታሪኩ ላይ ምንም ተፅዕኖ የላቸውም እኛም ይህንን መጠየቅ አያስፈልገንም፡፡ መሐመድ ያያቸው አራቱ ወንዞች በ‹ጳውሎስ ራዕይ› ላይ ያሉት ናቸው፡፡ ከዚህ በላይ የጠቀስነውን ስህተት የያዙት እነዚህም የኋለኞቹ ከኤደን ወንዞች ጋር ተመሳሳይ ናቸው፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ ወደ ሰማይ የመውጣት ዘገባዎች ማለትም የሄኖክ፣ የኤልያስ እና የጌታችን ማረጎችና፣ ‹ወደ ሦስተኛው ሰማይ መነጠቅ› የሚለው ሐሳብ፣ አንዳንዶች የሐዋርያው ጳውሎስን የሚጠቅስ ነው ብለው የሚገምቱት፣ እነዚህ ሁሉ ዘገባዎች እስካሁን ላገኘናቸው ተረቶች የመጀመሪያው ምንጮች አልነበሩም፡፡ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምንጭ አላቸው ማለት አስቸጋሪና ከጠቀስናቸው ከፐርሺያንና ከሕንዳውያን ተረቶች ጋር እነርሱን ማገናዘብ አላስፈላጊ ቢሆንም የእነርሱ ምንጭነት ግን እውነት ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ይህ ከሆነ ደግሞ የመሐመዳውያን የመሐመድ ወደ ሰማይ የመውጣት ተረት ልክ እንደሌሎቹ ተረቶች ሁሉ ስለ መሐመድ የተፈጠሩ ፈጠራዎች ናቸው፣ እነዚህም በሌሎቹ ተረቶች ሞዴልነት ማለትም በአርታ ቪራፍ ናማክ ውስጥ እንዳሉት የተቀመሩ ናቸው፡፡ ይህም እርሱን በአንዳንድ ሁኔታዎች ተመሳሳይ ነበር ለማለት በታቀደ ዕቅድ ውስጥ ቢሆንም እንኳን፣ ከክርስቶስና  ከእርሱ በፊት ከመጡት ከሌሎች ነቢያት ሁሉ የበለጠም ለማድረግ ነው፡፡

የአዘጋጁ ማሳሰቢያ፡-

 

በቁርአን ውስጥ የሚገኙት ትምህርቶችና ዘገባዎች ከሰማይ ሰሌዳ ላይ የወረዱ መሆናቸውን ብዙ ጊዜ የምንሰማ መሆናችን ምንም ጥርጥር የሌለው ነገር ነው፡፡ የቁርአን ዘገባዎች ከሰማይ ሰሌዳ ላይ የመጡ ከሆነ ከሌሎች አገሮች ተረቶችና ተራ የሆኑ ማለትም እውነት ከማይመስሉ ነገሮች ሁሉ መፅዳት ይጠበቅባቸዋል፡፡

የምዕራፍ አምስት የመጀመሪያ ክፍል የሚያስረዳን ቁርአንም ሆነ የሙስሊም ልማዶች የዞሮአስተርያውያን ፓጋናዊ እምነት ትምህርቶችና ተረቶች እንደተሰበሰቡባቸው ነው፡፡ ይህ ከዚህ በላይ እንደቀረበውና በተከታታይም እንደሚቀርበው በማስረጃ ከተረጋገጠ ደግሞ በምንከተለው እምነት ላይ ትልቅ ጥያቄን እንድንፈጥር ያደርገናል፡፡

ጠያቂ አዕምሮ ኖሮን ነገሮችን የበለጠ ለመመርመር መነሳት ደግሞ  ከሰው ልጅነት ባህርያት አንዱ ነው፡፡ ከዚህም በላይ እምነት ለጊዜው ወይም ለሰዎች ስንል ብቻ የምንከተለው ጉዳይ ሳይሆን የዘላለም ሕይወትን የሚነካ ጉዳይ ነውና በቀላሉ ሊታይ አይገባውም፡፡

በዚህ ድረ ገፅ ላይ በተከታታይ የሚቀርቡትን ጽሑፎች ለምትከታተሉ ሙስሊሞች ሁሉ አዘጋጆቹ የሚያሳስቡት ሁለት ነገሮች ላይ ትኩረት እንድታደርጉ ነው፡፡ አንደኛው፡ እምነታችሁ ከሞት በኋላ ስለሚኖረው የዘላለም ሕይወት የሚሰጣችሁ ተስፋ በእርግጥ ምን እንደሆነ እንድታስቡ፡፡ ሁለተኛ፡ ደግሞ በጥናትና በማስረጃ እየተረጋገጠ እንዳለው የምትከተሉት እምነት ከእግዚአብሔር የመጣ ካልሆነ ተስፋችሁ ምን ሊሆን እንደሚችል እንድታስቡ ነው፡፡

በመጨረሻም ክርስትያኖች የሚያምኑትን መጽሐፍ ቅዱስን እንድታነቡና መልእክቱን በቅንነት እንድትረዱትና የዘላለምን ተስፋ እንዴት እንደሚገልፀውና እርሱም እንዴት እንደሚገኝ ከክርስትያኖች እንድትጠይቁና እንድተረዱ እንጋብዛችኋለን፡፡

እኛን ወደ እውነቱ እንድንመጣ በፀጋው የረዳን እግዚአብሔር እናንተንም በፀጋው ይርዳችሁ አሜን፡፡

የትርጉም ምንጭ: THE ORIGINAL SOURCES OF THE QUR'AN 

ሙሉ መጽሐፉ በአማርኛ:  የቁርአን የመጀመሪያ ምንጮች

ለእስልምና መልስ አማርኛ  ዋናው ገጽ