የታረደው በግ

በአዘጋጁ

“ከዓለምም ፍጥረት ጀምሮ በታረደው በግ ሕይወት መጽሐፍ ስሞቻቸው ያልተጻፉ በምድር የሚኖሩ ሁሉ ይሰግዱለታል።” ዮሐንስ ራዕይ 13.8 

እውነተኛ ክርስትያኖች ሁሉ ክርስቶስ ኢየሱስን የሚያዩት እንደታረደ በግ ሆኖ ነው፡፡ ከላይ በተጠቀሱት ቃላት ውስጥ ግልጥ በሆነ መንገድ የክርስቶስ ኢየሱስ አጠቃለይ ባህርያት ቀርበዋል፡፡ ይህን እውነታ በተመለከተ በአዕምሮችን ውስጥ ግልጥ የሆነ መረዳት ልናገኝ ይገባናል፡፡ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ባህርያት በጣም በከበሩ መንገዶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተቀምጠዋል ለምሳሌም ያህል እንደ ንጉስ፣ ነቢይ ካህን እንዲሁም ጌታ ወዘተ፡፡

የታረደው በግ በመጽሐፍ ቅዱስ

ከሰላሳ ጊዜ በላይ ደግሞ እርሱ እንደ በግ ተደርጎ ቀርቧል፡፡ በመሆኑም እርሱ በዚህ ከላይ በተጠቀሰው አቀራረብ ውስጥ ለምን እንደዚህ ተደርጎ ተጠራ ብለን እንድንመረምርና እንድናጠና እንገፋፋለን፡፡ ብዙዎቻችን እንደምንስማማው ሁሉ ይህ አባባል ምሳሌያዊና በክርስትያኖች ዘንድ እጀግ በጣም የተወደደ ነው፡፡ በመሆኑም ክርስትያኖች “የበጉ ተከታዮች” ተብለው ተጠርተዋል፡፡  አንዳንዶች ፓራዳይዝ ወይንም ገነት በሚሉት በመንግስተ ሰማያት ውስጥም እውነተኛ ክርስትያኖች ከታደሉት ዕድል ውስጥ አንዱ “የሙሴንና የበጉን” ቅዱስ ዝማሬዎች ለመዘመር በመዘጋጀታቸው ጭምር ነው፡፡

ስለዚህም የሚከተሉትን ማለትም፡ “የታረደው በግ”፣ “የሚያድነው በግ”፤ “ተዋጊው በግ”፤ “በፅዮን ተራራ ላይ የቆመው በግ”፤ “የበጉ መዝሙር”፤ “የበጉ ሙሽራ ወይንም ሚስት”፤ “የበጉ የሰርግ እራት”፤ “የበጉ የሕወት መጽሐፍ”፤ “የበጉ ተከታዮች” እና በዘመናት ሁሉ እርሱን ይከተሉት ዘንድ እንዲችሉ ለሕዝቡ የሚቀርበው ጥሪ “እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ” የሚሉትን አነጋገሮች ስለ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ መጽሐፍ ቅዱስ ያቀርብልናል፡፡

ክርስትያኖች የክርስቶስን የመስቀል ላይ የመስዋዕትነት ሞትና ትንሳዔ በሚያከብሩበት በዚህ ወቅት ለአንባቢዎቻችን ትኩረት የምናቀርበው ነገር ክርስቶስ ጌታችን የታረደው በግ በመባል ከተሰጠው ስያሜ ላይ የክርስትናን መሰረታዊ እምነት ምንነት እንዲያስተውሉና የራሳቸውን ሕይወት እንዲመረምሩ ነው፡፡

የታረደው በግና የኃጢአት መስዋዕት

ለመሆኑ “የታረደው በግ” በመባል የቀረበው ስያሜ ምን ያመለክታል? ስያሜው መስዋዕትን የሚያመለክት ነው፡፡ ይህም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተያያዘው ከኃጢአት ይቅርታ ጋር፤ ለኃጢአት ከተከፈለ ዋጋ ጋር፤ በምንም ሊተመን ከማይችለው ከይቅርታ ዋጋ ጋር ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ ነገሮች እንደገና የሚያሳዩት ነገር ሰዎች የተላለፉትን እና ያፈረሱትን የእግዚአብሔርን ሕግ፣ ከዚያም የተነሳ የተነፈጉትን መብት፣ እና በእግዚአብሔር ላይ በማመፅ ያጠፉትን ጥፋት ሁሉ ነው፡፡

ሰው በኃጢአት በመውደቁ የእግዚአብሔርን ሕግ ጥሷል እግዚአብሔር በእርሱ ላይ እንዳይገዛው እምቢተኝነቱን አሳይቷል፡፡ እንዲሁም በራሱ ነፍስ ላይ መከራን አምጥቷል በሰው ዘርም ሁሉ ላይ ይህ የኃጢአት ችግር ተላልፏል፡፡ ለዚህ ደግሞ ምስክርና ማስረጃ የሚሆኑንን ነገሮች ለመፈለግ ብዙ ጥረት ወይንም ምርምር ማድረግ የለብንም፣ እኛ እራሳችን ማስረጃዎች ነን፡፡ የልባችን ክፋት፣ የየዕለት ምኞቶቻችን፣ ትዕቢታችን፣ እራስ ወዳድነታችን፣ ምቀኝነታችን፣ ጥላቻችን፣ በድብቅ ወይንም በሚስጢር የምንፈፅማቸው ኃጢአቶቻችን ወ.ዘ.ተ ምስክሮቻችን ናቸው፡፡

የሰው ልጅ በኃጢአት የወደቀ ስለመሆኑ የሚናገሩት የእግዚአብሔር ቃላት የመጀመሪያዎቹ ምዕራፎች በመቀጠል የሚያቀርቡት ነገር ለእግዚአብሔር ስለቀረቡት ተከታታይ መስዋዕቶች ነው፡፡ 

በእነዚያ የመስዋዕት አቅርቦቶች በኩል ግን ለኃጢአት ይቅርታን ማስገኛው መንገድ ተዘጋጅቷል፡፡ ለተጣሰውም የእግዚአብሔር ሕግ የሚሆነውን ቅጣት የሚወስደው ማለትም ፍርድን የሚቀበለው ቀርቧል፣ በሰው ኃጢአት ከተበደለውና ካዘነው እግዚአብሔርም ጋር ብቁ የሆነው መታረቂያ ተደርጓል፡፡ ስለዚህም መርዙና ማርከሻው፣ እርግማኑና በረከቱ፣ ሞቱና ሕይወቱ አብረው እርስ በእርስ በተቃረነ ሁኔታ ቆመዋል፡፡ በአዳም በኩል የተበላሹት ነገሮች ሁሉ፤ እንበልና ትርጉም ያለው ሕይወት፣ እግዚአብሔራዊ ህብረት እውነተኛ ሰላም እና እውነተኛ ደስታ በጌታ በኢየሱስ መስዋዕትነት እንደገና እንዲታደሱ መንገድ ተከፍቷል፡፡

ይሁን እንጂ ለብዙ ሺ ዓመታት በመለኮት የተመደቡት መስዋዕቶች በራሳቸው ምንም ዋጋ አልነበራቸውም “የፍየሎችና ኮርማዎች ደሞች” ጳውሎስ በትክክል እንደተናገረው በራሳቸው ኃጢአትን ለማስወገድ አይችሉም ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ከአዳም ጀምሮ እስከ ክርስቶስ መምጣት ድረስ ነበሩ፡፡

እነዚህ  በራሱ በእግዚአብሔር የተሰጡት ስርዓቶች በቤተመቅደሱ ውስጥ እንዲከናወኑ ታዝዘው ነበር፡፡ እነርሱም በራሱ በተመረጡ ካህናት ይቀርቡ ነበር ደማቸውም ለራሱ ክብር በተሰራው ቤተመቅደስ ውስጥ ይፈስሱ ነበር፡፡ በእነርሱም የኃጢአት ይቅርታ ይደረግና ሕዝቡም ከእግዚአብሔር ዘንድ ምህረትን ያገኝ ነበር፡፡

ነገር ግን እዚህ ላይ የሚመጣው ጥያቄ ይህ ይደረግ የነበረው እንዴት ነበር? በመሰዊያው ቢላዋ አማካኝነት በፈሰሰው ቁሳዊ ደም በኩል ነበርን? ወይንስ የመሰዊያውን ቀንድ በነካው ደም ነበርን? ወይንስ በቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ ባለው ታቦት ላይ በመረጨቱ ነበርን? የንፁሁና የታረደው እንሰሳ መሞት የቅዱስ እግዚአብሔርን ቁጣ ያበርደው ነበርን? ወይንስ በመሰዊያው ላይ በሚታረደው እንሰሳ ደም መፍሰስ የእርሱ ዓይኖች ይደሰቱበት ነበርን? የእነዚያ መስዋዕቶች ዋጋ በአገልግሎቱ ቁሳዊ ዋጋ ላይ ድርሻ ነበራቸውን? ለእነዚህ ሁሉ ጥያቄዎች መልሱን የምናገኘው ከዚህ በሚቀጥለው ዓረፍተ ነገር ውስጥ ነው፡፡

በእግዚአብሔር ትዕዛዝ ይቀርቡ የነበሩት እነዚያ መስዋዕቶች ሁሉ ዋጋቸውን ያገኙ የነበረው በቀራኒዮ መስቀል ላይ የተደረገውን አንዱንና ታላቁን መስዋዕት ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን እስከወከሉና እስካሳዩ ድረስ ብቻ ነበር፡፡ ስለዚህም እነዚያ ሁሉ መስዋዕቶች የክርስቶስ ኢየሱስን ሞት ወክለው ይቀርቡ ነበር፡፡

በመሆኑም መስዋዕቶች ሁሉ ወደ ክርስቶስ ኢየሱስ መስቀል ማለትም “የእግዚአብሔር በግ” ተብሎ ወደ ተጠራው “የታረደው በግ” ወደ ታረደበት መስቀል ላይ ይመለከቱ ነበር፡፡ በአስገራሚ ሁኔታ መስዋዕቶቹ ሁሉ የሚወክላቸውን ያገኙ የነበረው በዚህ በቀራኒዮ መስቀል ብቻ ላይ ነበር፡፡ በእርሱ በኩል ሁሉም ብቃት ይኖራቸው ነበር እንዲሁም መስዋዕት አቅራቢው ሰው ደግሞ የተሰዋው መስዋዕት እና የፈሰሰው ደም በወከሉት ተስፋ በተገባው በመሲህ መምጣት ላይ እምነት ይኖረው ነበር፡፡

የታረደው በግ፤ አንድ ጊዜ በራሱ መስዋዕትነት ኃጢአትን ከራሱ ሕዝብ ላይ ለማስወገድ በራሱ መስዋዕትነት በኩል የሚቆይ መንፈሳዊ በረከትን ለመስጠት መጣ፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ስለተመዘገቡት መስዋዕቶች የእግዚአብሔር ቃል ሲናገር “ቃየል ከአቤል ይልቅ ተቀባይነት ያለውን መስዋዕት በእምነት አቀረበ” ሲል አንደ አብርሃም ያሉት አባቶች ደግሞ መስዋዕትን በእግዚአብሔር መገለጥና ቃል መሰረት አቅርበው ነበር፡፡ እንዲሁም ባቀረቡት መስዋዕት ሁሉ ውስጥ ክርስቶስ መጥቶ ሲሰዋ ለማየት ይናፍቁ ነበር፡፡ ሐዋርያውም በቃሉ ላይ “እነዚህ ሁሉ በእምነት ሞቱ የተሰጠውን የተስፋ ቃል ሳያዩ ነገር ግን ከሩቅ ሆነው አዩት እንዲሁም አመኑ እናም በእምነት አቀፉት” ይላል፡፡

የታረደው በግና ልዩ ልዩ ጥያቄዎች፡

በሌዋውያን መጽሐፍ ውስጥ የቀረበውና በክርስቶስ ውስጥ ፍፃሜን ያገኘው ነገር ሎጂካልና እጅግ በጣም አሳማኝ ነገር ነው፡፡ በእርሱ ማለትም በክርስቶስ ውስጥ የእግዚአብሔር ምህረት ለሰዎች ሁሉ ቀርቧል ተሰጥቷልም፡፡ ክርስቶስ ኢየሱስን የማያሳይ ማንኛውም ደም መፍሰስ የነበረበት መስዋዕት ሁሉ ምንም ጥቅም ሊኖረው አይችልም ነበር፡፡ ይሆን የነበረውም ለነፍስ ምንም ጥቅም የሌለውና ለመጽሐፍ ቅዱሳዊው እውነት ደግሞ አሳፋሪ ነበር፡፡

ይሁን እንጂ እንደሚከተለው ዓይነት ጥያቄ ሊነሳ ይችል ይሆናል፡፡ እግዚአብሔር ከእራሱ ጋር የመታረቂያ ሌላ መንገድን ሊያዘጋጅ አይችልም ነበርን? ታላቁ እግዚአብሔር የንፁሃንን እንሰሶች ደም እንዲፈስ እና ቅዱስ መቅደሱን ምንም ነቀፋ በሌላቸው የበግ ግልገሎች ደም እንዲሞላ ሲያደርግ? ደግሞስ የራሱን ልጅ መስዋዕት አደረገ የሚለው ሃሳብ ምን ደስ ያሰኛል? እግዚአብሔርን ጨካኝ ባህርይ እንዳለው አድርጎ አያቀርበውምን? 

ይህንን ትልቅ ጉዳይ ጥቂት ቆም ብለን ልናስበው ይገባናል፡፡ ወሰን የሌለው ጥበብና እውቀት ያለው አምላክ እግዚአብሔር ከዚህ የተሻለ መንገድ አላገኘም ያለው ትክክለኛውና ብቁው መንገድ ይህ ብቻ መሆኑን ማወቅ ለእኛ በቂያችን ብቻ ሳይሆን እጅግ የምንደነቅበትም ነገር መሆን ይገባዋል፡፡ ስለዚህም ይህን መንገድ ወይንም እቅድ የማዘጋጀቱ እውነታ፤ ከእርሱ ጋር የመታረቂያው ብቸኛና የተሻለው መንገድ ይህ ብቻ መሆኑን በግልጥ ያሳየናል፡፡ ስለዚህም ይህንን በእርሱ ፊት እንደ አስፀያፊ ወይንም አሳዛኝ ነገር አድርጎ መቁጠር ተቀባይነት የሌለው ነገር ነው፡፡ በሌላ ጎኑ ግን ይህንን መለኮታዊ እውነታና እቅድ መረዳታችን እርሱን እጅግ በጣም በከበረ ክብር እንድናከብረውና እራሳችንን በፊቱ እንድናዋርድ ያደርገናል፡፡ ከዚህም በላይ የእኛን የቅድስና የንፅህና እንዲሁም የእውነት መረዳታችን እጅግ በጣም የተሻለ ይሆንልናል፡፡

ይህንን ነጥብ ለማብራራት የሚረዳን በኤደን ገነት ውስጥ አዳምና ከሔዋን በኃጢአት ሲወድቁ የነበረውን እውነታ ማወቅ ነው፣ እነዚያ የመጀመሪያዎቹ ሰዎች በኃጢአት ከወደቁ በኋላ ምን መደረግ ነበረበት? የእግዚአብሔር ሕግ ተጥሷል፤ የእግዚአብሔር ፍቅር ተጥሏል፤ እንዲሁም ይመጣባችኋል ተብሎ የተነገራቸው እርግማን በእነርሱ ላይ አሁን ተጣብቋል፡፡ ይህ ከሆነ በኋላ ወዲያውኑ፡-

ሰው ተፈጥሮበት የነበረው የእግዚአብሔር መልክ፤ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር የነበረው ኅብረት፤ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ይደሰትበት የነበረው ሰላም፣ ሰው ለእግዚአብሔር የነበረው ፍቅር፤ እንዲሁም እግዚአብሔርን በመታዘዝ ሁኔታ ውስጥ የተሰጠው የዘላለም ሕይወት የተስፋ ቃል ሁሉም ጠፍተው ነበር፡፡

የሰው ልጅ እራሱን ባስቀመጠበት በጥፋት ቦታ ላይ እግዚአብሔር ሊጥለው ይችል ነበር፣ የሰውን ልጅ እግዚአብሔር ቢፈርድበትና ለዘላለምም በሲዖል ውስጥ ቢጥለው ፍርዱ ፍፁም ትክክል ነው፡፡ የሰውን ልጅ ለመርዳት ወይንም ደግሞ ለማዳን እግዚአብሔርን ምንም የሚያስገድደው ነገር አልነበረም፡፡ በመሆኑም የሰው ልጅ ባለበት ሁኔታ ቢተወው ኖሮ የእግዚአብሔርን ፍፁምነት ምንም የሚነካው ነገር አልነበረም፤ እርሱ ቅዱስ ነው ንፁህም ነው፣ በፍርዱም የማያዛባ ነው፡፡

የመጀመሪያዎቹን ሰዎች እግዚአብሔር ለኃጢአታቸው ቢተዋቸው ኖሮ ወደ እርሱ ለመመለስ የሚያስችልን ነገር በራሳቸው ለማድረግ በፍፁም አይችሉም ነበር፡፡ በመሆኑም ወደ መለኮታዊ ምህረት እና ሞገስ የሚመለሱበት መንገድ አይኖራቸውም ነበር፡፡ ለፈረሰውም ሕግ መታረቂያ የሚሆን ምንም ነገርን ለማምጣት አይችሉም ነበር፣ በምንም መንገድ የዘላለምን ሕይወት ለማግኘት በፍፁም አይችሉም ነበር፡፡ ሆኖም ግን በኃጢአት እየቀጠሉ፣ የበለጠ እየዘቀጡና የዘላለም የፍርድ ጥፋት ውስጥ እስከሚገቡ ድረስ እየተበላሹ ሊሄዱ ይችሉ ነበር፡፡

የታረደው በግ አስፈላጊነት

እዚህ ላይ ነው “የታረደው በግ” አስፈላጊነት ግልፅ ሆኖ የሚመጣው፡፡ በእግዚአብሔር መለኮታዊ ፍቅርና ዕቅድ መሰረት እርሱ በራሱ የሕይወት ሰጪ ኃይል ሆኖ የጠፋውን የሰው ልጅ ለማዳን ወደ እኛ መጣ፡፡ ይህንንም ሲያደርግ የእግዚአብሔር መለኮታዊ ፍትህ የሚጠይቀውን ጥያቄ ምንም ሳይቀንስ፣ የእግዚአብሔርን ቅዱስ ሕግ በምንም መንገድ ሳይሽር ወይንም ሳያሻሽል በአጠፉት ሰዎች እጅ ውስጥ ምህረት ለማስቀመጥ መጣላቸው፡፡

የእርሱ መምጣት በመጀመሪያ እግዚአብሔር የገባው የተስፋ ቃልና በዘፍጥረት 3.15 ላይ “የሴቷ ዘር የእባቡን እራስ እንደሚቀጠቅጠው” የተነገረው የትንቢት ፍፃሜ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ከሴት የተወለደው አንዱ “የጥንቱን እባብ ሰይጣንን” እንደሚያጠፋው ነው፡፡ ከዚያም በኤደን ገነት ውስጥ በዚህ አታላይ ሰይጣን የተወሰደውን ግንኙነት እና የጠፋውን ሰላምና አንድነት በእርሱ ለሚያምኑት ሁሉ እንደሚመልሰው ነው፡፡ የተስፋ ቃል ኪዳኑ በመጀመሪያ ሲታይ በውጥኑ ደካማ፤ በአጠቃላይ አሰራሩ ጥቅል የሚመስል የነበረ ቢሆንም እንኳን ነገር ግን ታላቅ ዕቅድ ነበር፡፡ ስለዚህም ጊዜ እየሄደ የበለጠ እየተብራራና እየበራ እንዲሁም እየተጠናከረና በኃይልም እየጨመረ እስከ መሲሁ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ስጋ ለብሶ መምጣት ድረስ በእስራኤል አዕምሮ ውስጥ ዘልቆ በመግባት ተቀመጠ፡፡ ከእነርሱም አልፎ የሌሎችም በዓለም ውስጥ ያሉ ነገዶች ሁሉ ዋና ናፍቆትና ፍላጎት ሆነ፡፡

ስለዚህም በብሉይ ኪዳን ይቀርቡ የነበሩ መስዋዕቶች ይወክሉት የነበረው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ  የእግዚአብሔር በግ መጥቶ፣ በቅዱስነት፤ ያለምንም ነቀፋ በመሆን መታረዱን ነበር፡፡ ለዚህም ክቡርና ዋና ዓላማ ሲባል የሰውን ስጋ ለበሰ፣ ፍፁም አምላክ፤ የሰውን ስጋ ለብሶ ለሚያምኑበት መዳን ሲል በእነርሱ ምትክ በመስቀል ላይ ሞተ በመሆኑም በእነርሱ ላይ ሊመጣ የሚችለውን የሞትን ፍርድ ወሰደላቸው፡፡ ይህ አዲስ ዜና ነው፤ ይህ ዜና የክርስትና እምነት ለሰዎች የሚሰጠው ልዩ የሆነ ዜና ነው፣ ይህ የምስራች ቃል ነው፡፡ በዓለም ላይ ብዙ ሃይማኖቶች ቢኖሩም እንኳን ሰውን ለማዳን አምላክ የሰውን ስጋ ለብሶ እንደመጣና በሰው ልጅ ምትክ እንደሞተ የሚናገረው ክርስትና ብቻ ነው፡፡ ይህ ብቻ ነው ለሰው ልጅ መሰረታዊ የኃጢአት ችግር ትክክለኛና ዘለቄታዊ መልስ የሚሰጠው፡፡ ይህም የሚሆነው ይህንን ትልቅ አምላካዊ እቅድ ተገንዝቦ በግሉ አምኖ ለሚመጣው ሁሉ ነው፡፡ “የታረደውን በግ” ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን በቀራኒዮ መስቀል ላይ ተሰቅሎ ለኃጢአት መስዋዕትን ሲከፍል በእምነት ዓይነ ህሊናችን ስንመለከተው የሚከተሉት ሦስት ነገሮች ግልፅ ይሆኑልናል፡፡

አንደኛ የኃጢአት ሥራ፡

የኃጢአት ሥራ አስፈሪነትና አስቀያሚነት ይታየናል፡፡ የሰው ልጅ ኃጢአት ነው ክርስቶስን ከክብር ዙፋኑ ላይ ወደ እኛ እንዲመጣ ያደረገው፡፡ የሰው ኃጢአት ነው እርሱን የሀዘን ሰው ያደረገው፡፡ እኛን አሁን ባለንበት አሰቃቂ ክፋት እልቂት ጭከናና ጦርነት ሁኔታ ውስጥ የጣለን ኃጢአት ነው፡፡ ኃጢአት በእግዚአብሔ ፊት የተጠላ ነው፣ በኃጢአት ላይ ቅዱስ እግዚአብሔር በፅድቅ ፍርዱ የሚፈርድ መሆኑን ያሳየናል፡፡

ሁለተኛ የፍቅር ስራ፡

የታረደውን በግ በመስቀሉ ላይ ሆኖ ስናይ ሌላ የምናየውም ነገር የእርሱን የፍቅር ስራን ጭምር ነው፡፡ እኛ የሰው ልጆች በኃጢአት የተጨመላለቀ ሕይወት ያለን ነን፡፡ እኛ እራሳችንን ለኃጢአት ሸጠናል፣ በኃጢአት ውስጥ ዘቅጠናል፣ ጥላቻ፣ ነፍስ ግድያ፣ ስርቆት፣ ውሸት፣ አመንዝራ፣ ታሪካችንን ሞልቶታል፡፡ ከእነዚህ ከተጨማለቅንባቸው ኃጢአቶች የተነሳ ንፁህና ፍፁም የሆነው ፈጣሪ የሲዖልን ፍርድ ሊሰጠን ይገባዋል፡፡ የእርሱንም ፍርድ ብንቀበል  የሚገባን ነገር በትክክል የዘላለም ቅጣት ነው፡፡

ነገር ግን በመስቀል ላይ የታረደውን በግ ስንመለከት የእግዚአብሔርን ፍቅርና የምህረቱን ብዛት እንገነዘባለን፡፡ ፃድቅ እግዚአብሔር ፍርዳችንን በንፁህ ጌታ ኢየሱስ ላይ አድርጎ እኛን ለማዳን እርሱ በእኛ ምትክ እንዲታረድ አሳልፎ ሰጠው፡፡ ይህ ከኛ የተነሳ ሳይሆን ከእርሱ ፍቅር ብቻ የተነሳ እንደተደረገ ነው፡፡ ታዲያ ይህ ምን ዓይነት ፍቅር ነው፡፡ እኛን ጠላቶቹን እግዚአብሔር ወደደን ይህንን ፍቅር በቃላት ለመግለፅ አይቻልም፡፡ ምን ማድረግ ይገባናል? ማድረግ የሚገባን ይህንን የፍቅር ምህረት ለመቀበል ከኃጢአታችን ንስሀ በመግባት በመስቀል ላይ ስለ እኛ እራሱን በሰጠው በታረደው በግ በኩል ወደ እግዚአብሔር መቅረብ ነው፡፡ እግዚአብሔር ሙሉ ምህረትን ሊያደርግልን አዲስን ሕይወት ሊሰጠን የዘላለምም መንግስት ወራሽ ሊያደርገን ታማኝ እና ፃድቅ አምላክ ነው፣ ይህንንም ለማድረግ ቃል ኪዳንን ገብቶልናል፡፡

ሦስተኛ የዘላለም ዕቅድ፡

አንዳንዶች እንደሚያስቡት የጌታ ኢየሱስ ሞት በእርሱ ላይ የተደረገ ተፅዕኖ ይመስላቸዋል፡፡ አንዳንዶችም የእርሱን የመስቀል ሞት እንደ ድንገተኛ አደጋ አድርገው ሊቆጥሩት ያስባሉ፡፡ በዚህ ጽሐፉ መጀመሪያ ላይ የተጠቀሰው የራዕይ 13.8 የሚነግረን የተለየ ነገርን ነው፡፡ “ከዓለምም ፍጥረት ጀምሮ በታረደው በግ ሕይወት መጽሐፍ ስሞቻቸው ያልተጻፉ በምድር የሚኖሩ ሁሉ ይሰግዱለታል።” ጌታ ኢየሱስ የተሰቀለው የዛሬ ሁለት ሺ ዓመት በፊት ቢሆንም፤ ጽሑፉ ያቀረበው ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ እንደታረደ አድርጎ ነው፡፡ ይህ የሚያሳየው የእርሱ የመስቀል ሞት በእግዚአብሔር ጥንት የታቀደ፤ የታሰበበት፣ ነገር ግን ድንገተኛ በአደጋ ያልተፈፀመ መሆኑን ነው፡፡

በዓላማውም ውስጥ የተካተተው እና የተገለፀው የታረደው በግ መጽሐፍ እንዳለው፣ በመጽሐፉ ውስጥ ስሞቻቸው የተጻፉና ስሞቻቸው ያልተጻፉ ሰዎች መኖራቸውን ነው፡፡ በበጉ ማለትም በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ስራ አምነው ስሞቻቸው በመጽሐፉ ውስጥ ያልተጻፈላቸው ሰዎች፣ በዓለም ውስጥ ያለው መንፈስ ማለትም የሰይጣንና የተከታዮቹ አምላኪዎች ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ ለማንኛውም አስተዋይ አንባቢ ሁሉ በጣም ግልጥ ነው፡፡

ስለዚህም ይህንን ጽሑፍ ለምታነቡ አንባቢዎች እንድታስቡበት የምንመክረው፤ ክርስትያኖች የሚያከብሩት የክርስቶስ ስቅለትና የትንሳኤ በዓል ዋናው መልእክት በታረደው በግ ላይ መሆኑን ነው፡፡ መልእክቱም “የታረደ በግ” ሆኖ የተጠራው ጌታ ኢየሱስ እናንተንም ከኃጢአት ለማዳን መስዋዕት ሆኖ እንደተሰዋ እንድትገነዘቡ ነው፡፡ እርሱ ለሰው ልጆች ሁሉ መዳንና ከእግዚአብሔር ጋር መታረቂያ መንገድን ከፈተ፡፡ ይህ የሆነው ለክርስትያኖች ብቻ አይደለም ለእናንተም ጭምር ነው፣ ዓላማውም ከእግዚአብሔር እጅ በእርሱ አማካኝነት የዘላለም ሕይወትን እንድትወርሱ ነው፡፡ 

አሁንም ማስተዋል የሚገባችሁ ነገር ሃይማኖተኝነት፣ የሃይማኖትን ስርዓት መፈፀም ወይንም ልዩ ልዩ  ቅዱሳን የተባሉ የሃይማኖት ቦታዎች አካባቢ ጉዞ ማድረግ ከእግዚአብሔር ጋር ለመታረቃችንና ስንሞት መንግስተ ሰማይ ለመሄዳችን ዋስትና አይሰጡንም፡፡ በእግዚአብሔር ቃል ላይም አልታዘዙም፡፡ አንዱና እውነተኛው መታረቂያ መንገድ በታረደው በግ በኩል በእግዚአብሔር ፊት ቀርቦ ይቅርታን መጠየቅ ብቻ ነው፡፡

እኛ እንደምናውቀውና በሕይወታችንም እንደቀመስነው ይህ ውስብስብ እና አስቸጋሪ ነገር አይደለም፡፡ የሚያስፈልጉት ነገሮች ኃጢአተኝነታችንን ማመን፤ እራሳችንን የምናድንበት ምንም ነገር እንደሌለን መቀበል ከዚያም በእርሱ የመስዋዕትነት ሞት ማመንና ባለንበት ቦታ ሆነን ከልባችን ንስሀ በመግባት በእርሱ በኩል እግዚአብሔር ይቅርታ እንዲያደርግልን መለመንና በእርሱ ላይ መታመን ብቻ ነው፡፡ እግዚአብሔር ይርዳችሁ አሜን፡፡

 

ለእስልምና መልስ አማርኛ  ዋናው ገጽ