የቁርአን የመጀመሪያ ምንጮች

ምዕራፍ ሦስት ክፍል አራት

የሳቢያንና የአይሁዶች ሐሳቦችና ልማዶች ተፅዕኖዎች 

REV. W. ST. CLAIR TISDALL, M.A., D.D

ትርጉምና ቅንብር በአዘጋጁ

ሌሎች ሁኔታዎች

ቁርአን ከአይሁድ ተረቶች የተዋሳቸውን ሌሎች ነጥቦች ከዚህ በፊት እንዳደረግነው በሙሉ ዝርዝር መጥቀስ አንችልም፡፡ ለምሳሌም ያህል ከዮሴፍ፣ ከዳዊት እና ከሳዖል (ጣሉት) ጋር የሚዛመዱት ነገሮች ምርመራ፤ በቁርአን ውስጥ የተዘገቡት ዘገባዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ስለእነዚህ ሰዎች ከሚነገረን ጋር ምን ያህል እንደሚራራቁ ያሳያል፡፡ በሁሉም ባይሆንም በአብዛኛው ቁርአን ከመጽሐፍ ቅዱሳዊው ዘገባ የተለየበት ምክንያት የሚገኘው መሐመድ በእርሱ ጊዜ የነበረውን የአይሁድ ተረቶችን በመከተሉ ላይ ነው፡፡ ይህም በመጽሐፍ ቅዱስ ቃሉ ላይ የሚገኘውን የእነዚህን ሰዎች እውነተኛ ታሪክ ከመከተል ይልቅ የአይሁድን ተረት ተከትሏል፡፡ በአብዛኛዎቹም ጊዜያት ተረቶቹ እራሳቸው አልገቡትም ነበር፡፡ ስለዚህም ከግምት በመነሳት ወይንም ከሌሎች ምንጮች በመጠቀም እነርሱን አጋኗቸዋል፡፡ ነገር ግን ተረቶቹ ከሌሎች የተሰጡት ስለሆኑ የሌሎቹ ሁሉ ተረቶች ምሳሌዎች በመሆን ሊያገለግሉ ይችላሉ፡፡ አሁን እኛ የምንተላለፈው ቁርአን በግልፅ ባለ ዕዳ በሆነባቸው ወደ ሌሎች የአይሁድ ሁኔታዎች ላይ ነው፡፡  

የጡር ተራራ

በቁርአን 7.171 ላይ የሚከተለውን እናነባለን ‹የጡርን ተራራ ነቅለን ከበላያቸው እንደ ጥላ ኾኖ በአነሳነውና እርሱም በነሱ ላይ ወዳቂ መኾኑን ባረጋገጡ ጊዜ (አስታውስ) የሰጠናችሁን በብርታት ያዙ ትጠነቀቁም ዘንድ በውስጡ ያለውን ተገንዘቡ (አልን)፡፡› ጃላላይን እና ሌሎች መሐመዳውያን ተንታኞች ይህንን ጥቅስ የገለጡት እግዚአብሔር በሲናይ ተራራውን ከመሠረቱ እንዳነሳና የእስራኤል ልጆች በምድረ በዳ እያሉ ከራሳቸው በላይ እንደያዘው፣ ይህም የሆነው በሙሴ ሕግ ውስጥ ያለውን የማይቀበሉ ከሆነ በላያቸው ላይ እንደሚጥለውና እንደሚጨፈልቃቸው በማስፈራራት ነበር በማለት ነው፡፡ ምክንያቱም በጣም ልበ ደንዳኖች በመሆናቸው እነዚህን ሕጎች ከዚህ በፊት ለመታዘዝ አንፈልግም ብለው ነበር፡፡ ነገር ግን ይህን ማስጠንቀቂያ ሰምተው ሕጉን ተቀበሉ፡፡ ከዚያም በኋላ እግዚአብሔር ከዚህ በላይ የተጠቀሰውን ቃል ተናገረ፡፡ ተመሳሳይ የሆነ ተረት በቁርአን 2.60፣ 87 ላይ ተጠቅሷል፡፡

የዚህም ምንጭ በአይሁድ ትራክት ‹አቦዳህ ዛራ› ምዕራፍ 2 ቁጥር 2 ላይ ይገኛል፣ እዚያም የተነገረው በዚያን ሁኔታ (እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን ሲል የቀረበው) ‹እኔ እናንተን ከተራራው በላይ ልክ እንደ ክዳን ሸፈንኳችሁ (ጋረድኳችሁ)› በማለት ነው፡፡ ስለዚህም እንደዚሁ በሳባት (88፣1) የምናነበው ‹እነዚህ ቃላት ያስተምሩናል ቅዱሱ እርሱ የተባረከ ይሁን በእነርሱ ላይ ልክ እንደ ማሰሮ ተራራውን ገለበጠውና ለእነርሱ እንዲህ አላቸው ‹ሕጉን ከተቀበላችሁ ደህና ካልተቀበላችሁ ግን የእናንተ መቃብር በእዚያ ይሆናል›፡፡

በአምስቱ የሙሴ መጽሐፍት ውስጥ ይህንን የመሰለ ተረት ይኖራል በማለት ለመናገር በፍፁም አይቻልም ይሆናል፡፡ ይህ የመነጨው በአንድ አይሁዳዊ ተንታኝ ስህተት ነው፣ እርሱም በዘፀዓት 32.19 ላይ ያለውን ቃል ተሳስቶ ተረድቶታል፡፡ እዚያም ሙሴ ከተራራው ሁለቱን የድንጋይ ፅላቶችን በእጁ ይዞ በወረደ ጊዜ እስራኤላውያን የሰሩትን የወርቁን ጥጃ ሲያመልኩ እንደነበረ አያቸው፡፡ ባሳፋሪው ሁኔታ ላይ በመሆናቸው በጣም ተናዶ የድንጋይ ፅላቶቹን ከተራራው በታች ከእጁ ወርውሮ ሰባበራቸው፡፡ ዘፀዓት 19.17 የሚነግረን እግዚአብሔር ለሙሴ ሕጉን እየሰጠው እያለ ሕዝቡ ከተራራው በታች ቆመው ነበር፣ በሁለቱም ሁኔታ ሐረጉ የሚለው ከተራራው ‹ግርጌ› ወይንም ‹ስር› በማለት ነው፡፡ ነገር ግን ባለፉት ጊዜያት የነበሩት፤ ተዓምራት ወዳጆቹና ተታላዮቹ አይሁዶች ሐረጉን በተሳሳተ መንገድ ለመረዳት መረጡ፤ ከዚያም የተራራው መነሳት ተረት ተፈጠረ፤ ይህም ከተራራው ግርጌ የሚለውን ሐረግ ለመተርጎም በተደረገው ጥረት ነው፡፡ ይሁን እንጂ የዚህ የተራራው ከሰዎች እራስ በላይ የመያዙ ተረት በሚያስደንቅ ሁኔታ ከሒንዱዎች ተረት፤ ይህም ከሳስትራስ ሳንስክሪት ጋር ይዛመዳል፡፡ በዚያም የተነገረው ነገር ክርሺና የተባለው ጣዖት አምላክ የጎኩላን ሕዝብ ለመጠበቅ በመመኘት፣ የአገሩን ሕዝብ በጣም ከባድ ከሆነው የዝናብ ማዕበል ለመከለል ጎቫርዳና የተባለውን ተራራ ከድንጋያማ መሰረቱ መዝዞ አወጣው እርሱም ከተራራዎቹ ሁሉ ትልቁ የሚባለው ሲሆን ለሰባት ቀንና ሌሊት በጣቱ ጫፍ ላይ እንደ ጃን ጥላ በራሶቻቸው ላይ አንጠልጥሎ አጠላቸው፡፡ አይሁዶች ይህንን ታሪክ ከሒንዱዎች ተውሰውታል ብለን አንገምትም፤ በቁርአን ውስጥ እንደተጠቀሰው ግን መሐመድ ከአይሁድ ምንጭ የወሰደው መሆኑ እርግጠኛ ነገር ነው፣ ምክንያቱም አይሁዶች ‹ከተራራው ግርጌ› የሚለውን የዕብራይስጡን ቃል ታሪክ በማያስኬድ ስሜት በጥሬው እንዲቀበሉት ተመርተው ነበር ወይንም የተሳሳተውን ትርጉም ፈጥረውት ነበርና፡፡

የወርቁ ጥጃ

ይሁን እንጂ ይህ የእስራኤላውያንን የምድረበዳ ጉዞ በተመለከተ ቁርአን የተናገራቸው አስደናቂ ታሪኮች ውስጥ ይህ ብቸኛው አይደለም፡፡ ሙሴ በእስራኤላውያን መካከል ባልነበረበት ጊዜ ሰርተው ስላመለኩትም ጥጃ የተነገረን ተረት አስገራሚነቱ ዝቅተኛ አይደለም፡፡ በቁርአን ላይ የተነገረን ሙሴ ተመልሶ ስለዚህ ነገር ሲነቅፋቸው እነሱ የተናገሩት፡ ‹እኛ የሕዝቡን ጌጥ ሸክም ለመሸከም ተደርገን ነበር እናም ወደ እሳት ውስጥ ጣልናቸው ሳምራዊውም እንደዚሁ እሳት ውስጥ ተጣለ፣ ከዚያም እርሱ ለእነርሱ ጥጃን በአካሉ ለእነርሱ አመጣላቸው፡፡  በቁርአን 20፣87-88 የተነገረን ነገር ሙሴ ተመልሶ ስለዚህ ነገር ሲወቅሳቸው እነሱ የተናገሩት ነገር ‹ከሕዝቦቹ ጌጥ ሸክሞችን ተጫን (ተሸከምን) በእሳት ላይ ጣልናትም ሳምራዊውም እንደዚሁ ጣለ አሉት› ለእነርሱም አካል የኾነ ጥጃን ለርሱ መጓጎር ያለውን አወጣላቸው ...› የጃላላይን ማስታዎሻ የሚለው ጥጃው ስጋና ደም ሆኖ ነበር የተሰራው፣ እምቧ የማለትም ኃይል ነበረው ምክንያቱም ለእርሱ ሕይወት ተሰጥቶት ነበር እፍኝ በሚያክል አቧራ አማካኝነት ከመልአኩ ገብርኤል ቆሞበት ከነበረው ቦታ ማህተም ስር፣ ያንንም ሰማርያዊው ሰብስቦ በአፉ ውስጥ ጨመረው በቁጥር 96 መሰረት በተመሳሳዩ ቁርአን ምዕራፍ ውስጥ፡፡      

ይህ አፈታሪክ ከአይሁድ የመጣ ሲሆን፤ የሚረጋገጠውም ከሚከተለውና ከፕርቂይ ራባይ ኤሊዔዘር ቁጥር 45 ከተተረጎመው ማስረጃ ነው፡፡ እርሱም እንደሚከተለው ይላል፡- ‹ይህም ጥጃ እምቧ እያለ ወጣ፣ እስራኤላውያንም አዩት፡፡ ራባይ የሁዳህ እንዳለው ሳማኤል በውስጡ ተደብቆ ነበር እንዲሁም እምቧ ይል ነበር ይህም እስራኤልን ለማሳሳት ነበር›፣ ጥጃው እምቧ ማለት ችሎ ነበር የሚለው ሐሳብ ምንም እንኳን ከወርቅ የተሰራ ቢሆን ዘፀዓት 32.4 ሕያው ነበር እርሱ ከእሳት ወጥቶ ነበርና ቁጥር 24›፡፡ እዚህም ላይ እንደገና የምንመለከተው የምሳሌ አገላለጥ  በጥሬው እንዳለ በተወሰደበት ጊዜ ነው፡፡ የመሐመዳውያኑ ተንታኝ በቁርአን ውስጥ የሚገኘውን ‹የወይፈን አካል›፣ የሚለውን የሚገልጡት ወይፈኑ በትክክል ስጋና ደም የነበረው መሆኑን ያሳያል በማለት ተጨማሪ እርምጃን ወደፊት በማድረግና፣ እንሰሳው እምቧ ማለቱ እንዴት እንደነበረ ሲያስረዳ ነው፡፡ እዚህ ነጥብ ላይ መሐመድ የሚመስለው ብዙውን የአይሁድ ተረት በትክክል እንደተገነዘበው ቢሆንም ሳማኤል የሚለው ቃል ግን አስቸግሮታል፤ እንቆቅልሽም ሆኖበታል፡፡ ይህ ስም በአይሁዶች ዘንድ የሞት መልአክ ስም መሆኑን ባለመገንዘብ ምናልባትም አነባበቡን በመሳሳት እርሱ ቃሉን ‹ሳምሪ› ከሚለውና ትርጉሙም ‹ሳምራዊ› ከሆነው ጋር በስህተት አስገባው፡፡ ይህንን ስህተት በእርግጥ አድርጓል ምክንያቱም አይሁዶች ከሳምራውያን ጋር ጠላቶች እንደነበሩ ያውቃልና፡፡ የእርሱም ሐሳብ እነርሱ የጥጃውን መስራት ለሳምራዊያኖቹ እንዲያደርጉት በመመኘት ነበር፡፡ (ማለትም ሳምራውያን አደረጉት እንዲባል ፈልጎ ነበር)፡፡ ይህንንም ያለምንም ጥርጥር አረጋግጧል፡፡ በዚህ የሳምራውያን እምነት አንዳንድ የማይለዩ ስብስቦች መሠረት ሰማርያን ‹ኃጢአት እንድትሰራ አደረጋት› ስለተባለለት ስለ ንጉሱ ኢዮርብአም ሰምቷል፡፡ ‹ንጉሡም ተማከረ፥ ሁለትም የወርቅ ጥጆች አድርጎ። እስራኤል ሆይ፥ ወደ ኢየሩሳሌም ትወጡ ዘንድ ይበዛባችኋል፤ ከግብጽ ምድር ያወጡህን አማልክቶችህን እይ አላቸው።አንዱን በቤቴል፥ ሁለተኛውንም በዳን አኖረ።› 1ነገስት 12.28፣29፡፡ ነገር ግን በዚያን ጊዜ የሰማርያ ከተማ አልተገነባችም ወይንም ቢያንስ በዚያ ስም አልተጠራችም ነበር፡፡ ሙሴ ከሞተ ከብዙ መቶ ዓመታት በኋላ የመጣውን የሰማርያ ታሪክ ከዚህ ታሪክ ጋር በማያያዝ መሐመድ ምን ያህል ጊዜውን የሳተ መሆኑ መገንዘብ ቢያንስ ያስገርማል፣ በማንኛውም ሌላ መጽሐፍ ውስጥ የማይገኘው፣ በቁርአን ውስጥ ብቻ በተገኘበት ሁኔታ ውስጥ መገኘቱ እጅግ በጣም አስገራሚ ነው፡፡ የተገኘውም እንደ ሌሎቹ ብዙ ሁኔታዎች ሲሆን፣ የመሐመድ መጽሐፍ ቅዱስን አለማወቅ ነገር ግን ከአይሁድ ተረቶች ጋር መተዋወቅ በጣም ያስገርማል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደተጠቀሰው የወርቁን ጥጃ የሰራው አሮን መሆኑን መጠቆም እጅግ በጣም ጠቃሚ ነው፣ በታሪኩም ላይ እኛ የሳማኤልንም ሆነ ወይንም የሳምራዊውን ስም በፍፁም ተጠቅሶ አናገኝም፡፡

እንደገናም ደግሞ በቁርአን 2.54፣55 ላይ የተነገረን ነገር እስራኤላውያን ‹... ሙሳ ሆይ! አላህን በግልጽ እስከምናይ ድረስ ላንተ በፍጹም አናምንልህም ባላችሁም ጊዜ (አስታውሱ) እናንተም እየተመለከታችሁ መብረቅ ያዘቻችሁ፣ ከዚያም ታመሰግኑ ዘንድ ከሞታችሁ በኋላ አስነሳናችሁ› ቁርአን 2.55-56፡፡ እናም እነርሱ የእግዚአብሔርን መታየት እየተጠባበቁ ትኩር ብለው እያሉ መብረቅ መታቸውና ሞቱ፣ ነገር ግን ከሞቱ በኋላ እግዚአብሔር ወደ ሕይወት እንደገና አነሳቸው፡፡› አሁንም ይህ ተረት የተወሰደው ከአይሁዶች ነው ምክንያቱም የሳንሄድሪን ትራክት ቁጥር 5 ላይ የመለኮትን ድምፅ በመብረቅ ውስጥ ሲናገር ሰምተው ሞቱ፣ ነገር ግን ሕጉ እራሱ ስለ እነርሱ ማለደላቸውና እነርሱም ወደ ሕይወት እንደገና ተመለሱ ይላልና፡፡ ለእንደዚህ ዓይነት ተረቶች መሰረትን ለማግኘት ከተፈለገ በዕብራውያኖቹ ቃላት ውስጥ ዘፀዓት 20.19 ‹ሙሴንም። አንተ ተናገረን እኛም እንሰማለን፤ እንዳንሞት ግን እግዚአብሔር አይናገረን አሉት› ደግሞም ይህንኑ ሐሳብ (ዘዳግም 5.25) ላይም እንደገና ማግኘት ይቻላል፡፡

በሰማይ የተጠበቀው ሰሌዳ

ሙስሊሞች ሁሉ የሚያምኑት ገና ሰማይና ምድር ከመፈጠራቸው በፊት አስቀድሞ በሰማይ ላይ በተጠበቀው ገበታ (ሰሌዳ) ቁርአን ተጽፎ እንደሚገኝ ነው፡፡ የዚህም የእነሱ እምነት በቁርአን 85.21፣22 መሠረት ነው ‹ይልቁንም እርሱ የከበረ ቁርአን ነው፡፡ የተጠበቀ በኾነ ሰሌዳ ውስጥ ነው፡፡› በሚያስገርምም ሁኔታ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉት መዝሙራት እንደዚህ ጥንታዊነት እንዳላቸው አያምኑም፣ ደግሞም በቁርአን 21.105 ላይ እግዚአብሔር እንደተናገረ ሆኖ የቀረበው ‹ምድርንም መልካሞቹ ባሮች ይወርሷታል ማለትን ከመጽሐፉ (ከተጠበቀው ሰሌዳ) በኋላ በመጽሐፎቹ በእርግጥ ጽፈናል፡፡› የሚል ነው፡፡ ለዚህም ማጣቀሻው ‹ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፥ በብዙም ሰላም ደስ ይላቸዋል። ... ከክፉ ሽሽ፥ መልካምንም አድርግ፤ ለዘላለምም ትኖራለህ› መዝሙር 37.11፣29 ነው፡፡ በቁርአን ውስጥ ሕግ፣ መዝሙራት እና ወንጌል ስማቸው የተጠቀሱባቸው 131 የሚሆኑ አንቀፆች ቢገኙም እንኳን፣ ከብሉይ ኪዳን ውስጥ ተጠቅሶ የሚገኘው ብቸኛ ጥቅስ ይህ ብቻ ነው፡፡ በ131 አንቀፆች ውስጥ የተጠቀሱት ሕግ፣ መዝሙራትና ወንጌላት ከሰማይ እንደወረዱና በእግዚአብሔር ነቢያትና በሐዋርያቱ የተላኩ እንደነበሩ በሚያረጋግጥ ሁኔታ ነው፡፡ ለብዙዎች ሰዎች አንድ መጽሐፍ በሚገባ ካልተጠረዘና ካልተቀናበረ በስተቀር እንደ አንድ የስልጣን ምንጭ ሊጠቀስና ማስረጃ ሆኖ ሊቀርብ በፍፁም አይችልም፣ ስለዚህም የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ቁርአን ከመኖሩ በፊት የግድ ነበረ ማለት ነው፡፡ በእርግጥ እኛ ይህንን እውነታው ከታሪክ እንረዳዋለን፡፡ ነገር ግን ለሙስሊሞች ይህ እውነታ እንደ ትልቅ ነገር ሲወሰድ አንመለከተውም፣ ቁርአን ከመሐመድ በፊት የነበረ ነው፣ በሰማይ ሰሌዳ ላይ ተጽፎ ነበር ከሚሉት ሐሳባቸው ጋር አሁንም ይጣበቃሉ፡፡

ስለዚህም እኛ አሁን የምንሻገረው ተቀባይነት ያለው የእነርሱ ልማድ ስለ እነዚህ አንቀፆች ምን ይላል? ወደሚለው ጥያቄያችን ነው፣ ለዚህም የሚሆንን መልስ የምናገኘው ቂሳሱል አንቢያ ገፅ 3ና 4 ላይ ባለው ገለጣ ነው፡፡ እግዚአብሔር ነገሮችን ሁሉ እንዴት እንደፈጠራቸው በሚያስረዳው ገለጣ (ዘገባ ወይንም ጽሐፍ) ውስጥ የተጠቀሰው ስራ ያቀረበው ‹ከዙፋኑ ስር (ወይንም ከከፍተኛው ሰማይ) እርሱ ዕንቁን ፈጠረ፣ ከዕንቁም የተጠበቀውን ሰሌዳ ፈጠረ የእርሱም ከፍታ 700 ዓመታት ጉዞ ነበር ስፋቱም ደግሞ 300 ዓመታት ጉዞ ነበር፡፡ ዙሪያው ደግሞ በታላቁ እግዚአብሔር ኃይል በቀይ ቀለም ያጌጠ ነበር፡፡ ከዚያም ለብዕር ትዕዛዝ መጣለት ‹በፍጥረቴ ውስጥ ያለውን እውቀቴን ጻፍ እስከ ትንሳዔ ቀን ድረስ የሚዘልቀውን እውቀቴን ጻፍ› ተባለ፡፡ በመጀመሪያም በተጠበቀው ሰሌዳ ላይ የጻፈው፣ ‹አዛኝና ርህሩህ በሆነው እግዚአብሔር ስም፡፡ እኔ እግዚአብሔር ነኝ ከእኔም ሌላ አምላክ የለም፡፡ ለእኔ ትዕዛዝ እራሱን ያስገዛ ምንም ቢኖር እንዲሁም በእርሱ ላይ በማመጣው ክፉ ነገር ታጋሽ የሆነና ለሞገሴ ደግሞ አመስጋኝ የሆነውን እኔ የእርሱን ስም እጽፈዋለሁ፣ ከእውነተኞችም ጋር አነሳዋለሁኝ፤ በትዕዛዜ የማይደሰት፣ በእርሱ ላይ በማመጣው ክፉ ነገር የማይታገስ፣ ለእኔም ፀጋ ምስጋናን የማይሰጥ ማንም ቢኖር፣ እርሱ ከእኔ ሌላ ለእራሱ ሌላ ጌታን ይፈልግ ከእኔም መንግስተ ሰማያት እርሱ ይውጣ፡፡ በዚህም መሰረት ብዕሩ የታላቁን እግዚአብሔርን የፍጥረት እውቀት እስከ ትንሳኤ ድረስ እንዲሆን የፈቀደውን ሁሉ ጻፈ፣ የዛፍ እንቅስቃሴን ሁሉ መውረድን ወይንም መውጣትንና ሌላውንም ነገር ሁሉ በታላቁ እግዚአብሔር ኃይል ጻፈ›፡፡

የተጠበቀው ሰሌዳ የሚለው ሐሳብ እራሱ የተወሰደው ከአይሁዶች ነው፡፡ በዘዳግም መጽሐፍ ውስጥ የተነገረን ነገር ሙሴ በእግዚአብሔር ትዕዛዝ የተሰበሩትን የቀደሙትን የመሰሉ ሁለት የድንጋይ ጽላቶችን እንዲቀርፅ ሲነገረውና እግዚአብሔርም አስርቱን ቃላት እንደጻፈባቸው በዘዳግም 10.1-5 ላይ እናነባለን፡፡ ከዚያም ሙሴን ከግራር ወይንም ሺቲም ዛፍ በተሰራ ሳጥን ውስጥ እንዲያስቀምጣቸው አዘዘው፡፡ ሰሌዳ (ፅላት) የዕብራውያኑ ቃል ከአረብኛው ጋር አንድ ዓይነት ቃል ነው፡፡ ከ1ነገስት 8.9 እና ዕብራውያን 9.3፣4 ላይ የምንማረው ነገር እነዚህ ሁለት ፅላቶች ሙሴ በእግዚአብሔር ትዕዛዝ መሠረት በሰራው በታቦቱ ውስጥ ተቀምጠው እንደነበር ነው፡፡ ከዚህ እውነታ በመነሳት፣ በእግዚአብሔር የተጻፈና ትዕዛዛትን ይዞ በእርሱ ኃይል በሰማይ ላይ የተቀመጠ ፅላት አለ የሚለው ዘገባ ቀስ በቀስ በአይሁዶች መካከል ተሰራጨ ከዚያም በመሐመዳውያን ተወሰደ፡፡ ከዚህ በላይ እንደተጻፈው የቁርአን 85.21፣22 ቋንቋ በመሐመድ አዕምሮ ውስጥ አንድ ብቻ ሳይሆን ቢያንስ ሁለት ‹የተቀመጡ ሰሌዳዎች› ለመኖራቸው እርግጥ ነበር፣ ምክንያቱም በአረብኛ ‹የተጠበቀው ሰሌዳ› (ከብዙዎች አንዱ) እንጂ ‹ሰሌዳዉ› (አንዱ ብቻ) አይደለምና፣ ይህም በአሁኑ ጊዜ ያሉት መሐመዳውያን እንደሚገነዘቡትና እንደሚናገሩት አይደለም፡፡ ስለዚህም ሙሴ ያዘጋጃቸውና በታቦቱ ውስጥ ያስቀመጣቸው ሁለት የድንጋይ ፅላቶች ማገናዘቢያ መኖር ነበረበት፡፡ እግዚአብሔር በሕዝቡ መካከል መኖሩን የሚያመለክቱት ፅላቶች በታቦቱ ውስጥ እንደተቀመጡ ሁሉ፣ በእግዚአብሔር ፊት የተቀመጡ ናቸው በማለት የመናገር ልማድ ያስኬድ ነበር፡፡ ስለዚህም በሰማይ የተጠበቁ ሰሌዳዎች አሉ የሚለው ቀልድ ወይንም ተረት እምነቱና ምንጩ ከየት እንደሆነ ለመረዳት አሁንም አያዳግትም፡፡

ይሁን እንጂ ቁርአን በሰማይ በተጻፈው ሰሌዳ ላይ ተጠብቋል ብሎ መሐመድ የተናገረው ለምንድነው? ይህንን ጥያቄ ለመመለስ አሁንም አይሁዶችን መጠየቅና እነሱ በመሐመድ ጊዜ እና ከዚያ ቀደም ብሎ በሁለቱ ሰሌዳዎች ላይ ምን ተጽፎና በታቦቱ ውስጥ ተቀጧል ተብለው እንደተማሩ መገንዘብ አለብን፡፡ የዘዳግም መጽሐፍ አስርቱ ቃላት ብቻ በሰሌዳ ላይ ተጽፈው በታቦቱ ውስጥ መቀመጣቸውን በግልጥ ይናገራል፡፡ ከጊዜ በኋላ ግን የብሉይ ኪዳን መጻሐፍት በሙሉ እንዲሁም የታልሙድ መጻሕፍት በሙሉ በእነሱ ላይ ተጽፈውባቸው ነበር ወይንም ከእነርሱ ጎን ተቀምጠው ነበር የሚለው እምነት ተፈጠረ፡፡ ቅዱስ መጽሐፎቻቸውን ከሚያነቡት አይሁዶች ይህንን ንግግር መሐመድ በሰማ ጊዜ፣ የእርሱም መገለጥ በሰማይ ተጽፈው ከተቀመጡት አንድ ወይንም ሌሎች ሰሌዳዎች ላይ የመጣ ነው ማለቱ ይጠበቃል፡፡ ካልሆነ ግን ከብሉይ ኪዳን ስልጣን ጋር እኩል የሆነ ስልጣን አለው ለማለት በፍፁም አይችልም ነበር፡፡ ‹የተጠበቀ ሰሌዳ› የሚለው አባባል ምን ማለት እንደሆነ ምናልባትም ሙስሊሞች አይረዱት ይሆናል፣ ሆኖም ግን ከዚህ በላይ የጠቀስነውን አስገራሚ ታሪክ ቀስ በቀስ ፈጠረ፡፡

አይሁዶች ስለ ሰሌዳዎቹ ይዘት የተማሩትን ለማረጋገጥ ማየት የሚኖርብን በራኮት ከተባለው ትራክት ላይ ነው (እጥፋት 5 አምድ 1)፡፡ እዚያም የምናነበው ‹ራባይ ስምዖን ቤን ላኪሽ የተናገረው፡ ‹‹የተጻፈው እርሱ ምንድነው፣ ‹የድንጋይን ፅላት ሕጉንና ትዕዛዛቱን የጻፍኩትን እኔ እሰጥሃለሁ አንተም እንድታስተምራቸው› ዘፀዓት 24.12፡፡ ፅላቶቹ እነዚህ አስርቱ ቃላት ናቸው፣ ህጉ፣ የሚነበበው፣ እና ትዕዛዛቱ፣ ይህ ሚሽናህ ነው እርሱም እኔ የጻፍኩት ነው፣ እነዚህ ናቸው ነቢያት እና ቅዱሳት ጽሑፎች፡ አንተም እንድታስተምራቸው ይህም የሚያሳየው ጌማራን ነው፡፡ ይህም እነዚህ ሁሉም ለሙሴ ከሲና ተራራ የተሰጡ መሆናቸውን ያስተምራል፡፡›› የሚልን ነው፡፡

በአሁኑ ጊዜ ያለ ማንኛውም የተማረ አይሁዳዊ ከዚህ በላይ የጠቀስነውን ጥቅስ፤ ይህን የማይረባ ገለፃ ወዲያ መተው ወይንም መጣል እንዳለብን ይቀበላል፣ ምክንያቱም ሚሽናህ የተጠናቀረው በክርስትና ዘመን 200 ዓ.ም ሲሆን የኢየሩሳሌሙ ጌሜራ ደግሞ በ430 ዓ.ም ነው፣ የባቢሎናውያን ጌሜራ ደግሞ 53 ዓ.ም ገደማ ነውና፡፡ ነገር ግን ሙስሊሞች ይህንን አያውቁም፣ የሚመስሉትም እንደዚህ ዓይነቶቹን ሐሳቦች በብልጠት እንደ እውነት እንደተቀበሉና በቁራናቸውም ውስጥ ደግሞ እንደ ተጠቀሙበት ነው፡፡

ቁርአን በሰማይ ከተጠበቀው ሰሌዳ ላይ ነው የመጣው የሚለው አፈ ታሪክ ከአይሁድ ምንጭ የመጣ መሆኑን የሚያስረዳውን ነገር ለማጠቃለል የሚቀረው ነገር የፒርቂይ አቦት ምዕራፍ 5 ቁጥር 6 መጥቀስ ብቻ ነው፡፡ በዚያም ጽሑፍ ውስጥ የተገለጠው ነገር፤ ‹የሕጉ ሁለት ሰሌዳዎች ከሌሎች ዘጠኝ ነገሮች ጋር ዓለም በተፈጠረችበት ጊዜና የመጀመሪያው ሰንበት ከመጀመሩ በፊት ጠዋት ፀሐይ ስትወጣ ተፈጥረው ነበር› ይላል፡፡

ቃፍ ተራራ

በመሐመዳውያን አፈታሪክ ውስጥ ቃፍ የሚባለው አስደናቂ ተራራ በጣም ጠቃሚ ስፍራ የያዘ መሆኑ በጣም የታወቀ ነው፡፡ ቁርአን 50 እራሱ ቃፍ በሚለው ፊደል ነው የጀመረው፡፡ ስለዚህም የፊደሉ ስም የተጠቀሰውን ተራራ ስም እንደሚጠቅስ ተሰንዝሯል፡፡ ተንታኙ አባሲ ይህንን ገለጣ ይቀበለውና ይህንንም ለማስረገጥ በኢብን አባስ በኩል የመጣውን ልማድ ይጠቅሳል፡፡ ኢብን አባስ፡ ‹ቃፍ ምድርን የከበበ አረንጓዴ ተራራ ነው፣ የሰማዩም አረንጓዴነት የመጣው ከእርሱ ነው፣ በእርሱም እግዚአብሔር ይምላል› ብሏል፡፡ ስለዚህም በአራይሱል ማጃሊስ በሚከተሉት ቃላት ውስጥ እንደሚከተለው በሚገባ ተገልጧል ‹‹ታላቁ እግዚአብሔር የከበረ የአረንጓዴ ድንጋይ ተራራን ፈጠረ፡፡ የሰማይም ታላቅነት በእሱ የተነሳ ነበር፡፡ እርሱም ቃፍ ተራራ ተባለ ሁሉንም ይከብብ ነበር› (ምድርን በሙሉ)፡፡ ‹እናም እርሱ እግዚአብሔር በእርሱ የሚምልበት ነበር እርሱም እንዲህ ብሏልና ‹በቃፍ በከበረው ቁርአን›፡፡ በቂሳሱል አነቢያ ደግሞ አንድ ቀን ‹አብዱላህ ኢብን ሳላም መሐመድን የጠየቀው፣ በምድር  ላይ ያለው ከፍተኛው ተራራ ጫፍ ማነው በማለት ነበር፡፡ መሐመድም አለ ‹ቃፍ ተራራ ነው›፡፡ ከዚያም ቀጥሎ ስለዚህ ተራራ የተጠየቀውን ጥያቄም በመመለስ መሐመድ የመለሰው እንደሚከተለው ተቀምጧል፡ ‹ከአረንጓዴ የከበረ ድንጋይ ነው፣ የሰማዩም አረንጓዴነት ከእርሱ የተነሳ ነው› ጠያቂውም የእግዚአብሔር ነቢይ በዚህ ጉዳይ ላይ እውነት የተናገረ መሆኑን በመግለጥ ቀጥሎም እንዲህ አለ፡ ‹የቃፍ ተራራ ርዝመት ምን ያህል ነው?› በማለት ጠየቀ፡፡ መሐመድም የመለሰው ‹የእርሱ እርዝመት የ500 ዓመታት ጉዞ ርዝመት ነው› በማለት ነው፡፡ አብዱላህም ጠየቀ ‹ዙሪያው ምን ያህል ይርቃል?› የ2000 ዓመት ጉዞ ይርቃል በማለት መለሰ፡፡ የሙስሊም አፈታሪክ የተሞላበትን ስለዚህ አስገራሚ የተራራዎች ሰንሰለት ወደተነገሩት ወደ ሁሉም ሁኔታዎች ውስጥ መግባት አያስፈልገንም፡፡

የዚህን አፈታሪክ ምንጭ ጅማሬ እንደዚህ ዓይነት የተራራ ሰንሰለቶች ስለመኖራቸው መልሱ የሚገኘው በሐጊጋ 11 ቁጥር 1 ማገናዘቢያ ላይ ነው፡፡ እዚያም በዘፍጥረት 1.2 ላይ ባለው ‹ቶሁ› በሚባለው በጣም ጥቂት የሒብሩ ቃል መግለጫ ላይ ነው፣ የተጻፈውም፡ ‹ቶሁ ምድርን በሙሉ የሚከብ አረንጓዴ መስመር ነው፣ ከእርሱም ጨለማ ይወጣል›፡፡ መስመር የሚለው የሚገልጠው የዕብራይስጥ ቃል ግን ‹ቃን› የሚል ነው፡፡ መሐመድና ደቀመዛምርቱ ይህንን ‹ቃን› የሚለውን የሒብሩ ቃል ከሰሙ በኋላና መስመር እንደሚል ሳያውቁ ያለምንም ጥርጥር ያስተማሩት ይህ ዓለምን ሙሉ የሚከብብና ከእርሱም ጨለማ የሚወጣበት ታላቅ የተራራ ሰንሰለት ‹ቃን› ወይንም ‹ቃፍ› ተብሎ እንደሚታወቅ ነው፡፡ ይሁን እንጂ የጂዖግራፊ ተመራማሪዎች ዓለምን ሁሉ አስሰው በመሐመዳውያን ልማድ የተገለጠውን የተራራ ሰንሰለት ገና አልደረሱበትም ማለት በፍፁም አይቻልም፡፡

ከእነዚህም በተጨማሪ በቁርአንና በእስላማዊ ልማዶች ውስጥ መግቢያ በር ያገኙትን በጣም በግልጥ ከአይሁድ የመነጩ ሌሎች ጥቂት ሐሳቦችን መጥቀስም ግድ አለብን፡፡

ሰባት ሰማያት

በቁርአን 17.44 ላይ ‹ሰባቱ ሰማያትና ምድርም በውስጣቸውም ያለው ሁሉ ለርሱ ያጠራሉ ከነገርም ሁሉ ከማመስገን ጋር የሚያጠራው እንጂ አንድም የለም ግን ማጥራታቸውን አታውቁትም እርሱ ታጋሽ መሓሪ ነው፡፡› በዚህ ጥቅስ ሰባት ሰማያት ተጠቅሰዋል በቁርአን 15.44 ላይ ‹ለርሷ ሰባት ደጃፎች አሏት ለየደጃፉም ሁሉ ከነሱ የተከፈለ ፋንታ አለ› በሚለው ደግሞ ለሲዖል ሰባት ደጃፍ (በር) እንዳሏት ይናገራል፡፡ እነዚህ ሁለቱም አረፍተ ነገሮች የመጡት ከአይሁድ ልማድ ውስጥ ነው፡፡ የመጀመሪያው በሃጊጋ ምዕራፍ 9 ቁጥር 2 ውስጥ ሲገኝ ሁለተኛው ደግሞ በዞሃር ምዕራፍ 2. ቁጥር 150 ይገኛል፡፡ ይህ አስገራሚ ነው፣ ሂንዱዎች ከምድር ገፅ በታች ሰባት ዝቅተኛ ደረጃዎች አሉ በማለት ያምናሉ፣ ከዚያም በላይ ሰባት ከፍተኛ ፎቆችን ለማለትም ይቻላል፣ ሁሉም ያረፉት እጅግ በጣም ትልቅ በሆነ እባብ ጭንቅላት ላይ ነው፣ የእርሱም ስም ሴሻ ሲሆን እርሱም አንድ ሺ እራሶች አሉት፡፡ ሰባቱም ሰማያት ያለምንም ጥርጥር ወይንም ቢያንስ ከፀሐይ ክበብ፣ ከጨረቃ፣ እና ከፕላኔት ሜርኩሪ፣ ቬነስ፣ ማርስ፣ ጁፒተርና ሳተርን ጋር አንድ ዓይነት ናቸው፡፡ እነዚህም በመሐመድ ጊዜ በምድር ዙሪያ ይዞራሉ ተብሎ ይታመን ነበር፡፡ በመሐመዳውያን ልማድ መሠረት ምድር ከሰባት ፎቆቿ ጋር ያረፈችው ካጁታህ በሚባል ወይፈን ቀንዶች መካከል ነው፣ እርሱም 4000 ቀንዶች አሉት፣ እያንዳንዱም ከሌላው የ500 ዓመታት ጉዞ ርቀት ያለው ነው፡፡ እርሱም እንደ ቀንዶቹ ብዙ ዓይኖችና ብዙ የሆኑ አፍንጫዎች አፎችና ምላሶች አሉት፡፡ የእርሱም እግሮች የቆሙት በአሳ ላይ ነው እርሱም በውሃ ውስጥ የአርባ ዓመት ዋናን ወደ ጥልቁ ውስጥ አድርጓል፡፡ ሌላው ምንጭ የተናገረው ደግሞ ምድር በመጀመሪያ ደረጃ በመልአክ እራስ ላይ ነበር ያረፈችው፣ የዚህም መልአክ እግሮች ያረፉት እጅግ በጣም ትልቅ በሆነ የሩቢ አለት ላይ ነው እርሱም የተደገፈው በወይፈን ነው፡፡ የዚህ የምድርና የወይፈን ግንኙነት ሐሳብ ምናልባትም የአሪያን ምንጭ ሳይኖረው አይቀርም፡፡ ምድር ሰባት ፎቆች እንዳሏት አድርጎ የሚያቀርበው አፈታሪክ ምናልባትም እርሷ ሰማይን ትመስላለች በማለት ለማቅረብ ከታሰበ ፍላጎት የመነጨ ሳይሆን አይቀርም፡፡ እርሱም የመነጨው በአቫስታ ውስጥ የሚገኘውን ምድር ሰባት ካርሸቫሮችን ወይንም ታላላቅ ክፍሎች አሁንም የሚነገረውንና ‹ሰባት የአየር ፀባዮችን› ከሚለው የፋርሳውያንን አረፍተ ነገር በተሳሳተ መንገድ በመረዳት ሳይሆን አይቀርም፡፡ ስለዚህም በየሽት 19 ቁጥር 31 ላይ፤ ይማ ክሺያታ ወይንም ጃምሺድ የተነገረው ‹በምድር ሰባት ክፍሎች ላይ እንደገዛ ነው›፡፡ ይህም እንደገና የሚያያዘው ከሂንዱዎች ጂኦግራፊ ከቪፓስ ጋር ነው፡፡ ስለዚህም ከሰባቱ የመጀመሪያው ካርሸቫሮች ከፍተኛ ተራራ እንደበረና ሌሎቹ ደግሞ በስሩ ነበሩ ለማለት ካልሆነ በስተቀር፣ አንዱ በአንዱ ላይ ተነባብረው ነው ያሉት በማለት መገመት ወይንም መመኘት ስህተት ይሆናል፡፡

የእግዚአብሔር ዙፋን

በቁርአን 11.7 ላይ የእግዚአብሔርን ዙፋን በተመለከተ የተነገረው ሰማይና ምድር ከመፈጠራቸው በፊት ‹ዐርሹም በውሃ ላይ ነበር› (በአማርኛው ቁርአን ዐርሹ የሚለው ቃል ዙፋን ለሚለው የተሰጠ ትርጉም ነው)፡፡ ልክ እንደዚሁም ዘፍጥረት 1.2 ላይ ትንተና የሰጠው አይሁዳዊው ተንታኝ ራሺ፣ በጣም የታወቀውን የአይሁድ ልማድ ተንተርሶ እንደዚህ ጻፈ፤ ‹የክብር ዙፋን በአየር ላይ ቆመ እናም በውሃው ላይ ተንሳፍፎ ነበር›፡፡

የሞት መልአክ

የመሐመዳውያን ጸሐፊዎች የነገሩን ነገር ማሊክ የሚባለውና በቁርአን 43.77 ‹ማሊክ ሆይ! ጌታህ በኛ ላይ (በሞት) ይፈረድ እያሉ ይጣራሉም እናንተ (በቅጣቱ ውስጥ) ዘላለም ነዋሪዎች ናችሁ ይላቸዋል› በሚለው ላይ ያለው መልአክ በቁርአን 74.30 ላይ ‹በርሷም ላይ አስራ ዘጠኝ (ዘበኞች) አሉባት› ለተባሉት 19 የሲዖል ጠባቂ መላእክት አለቃ ሆኖ ተሾሟል፡፡ አይሁዶችም ልክ እንደዚሁ ብዙውን ጊዜ ‹የሲኦል ልዑል› ስለሆነ መልአክ ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን ሙስሊሞች ማሊክ የሚለውን ስም ሞሎክ ከሚለው ስያሜ ተበድረውት ነው ይህም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከነዓናውያን ጥንት ለእርሱ ክብር ሰዎችን ከነሕይወታቸው በእሳት በመሰዋት የሚያመልኩት አንዱ የጣዖት አምላካቸው ስም ነው፡፡ ቃሉም በአረብኛና በሒብሩ ግሳዊ ቅፅል ሆኖ የሚያገለግል ሲሆን ትርጉሙም ‹ገዢ› ማለት ነው፡፡

በመንግስተ ሰማይናሲዖል መካከል ያለው መጋረጃ  

በሱራ 7.46 ላይ በመንግስተ ሰማይና በሲዖል መካከል ይህ ምዕራፍ በተጠራበት ስም የተሰየመ መጋረጃ ይገኛል፡፡ በእርግጥም እርሱ ይህንን ስያሜ ያገኘው አል አራፋት ከሚለው መጠሪያ ነው፡፡ ‹በመካከላቸውም (1) ግርዶሽ አልለ፣ በአዕራፍም ላይ (2) ሁሉንም በምልክታቸው (3) የሚያውቁ ሰዎች አልሉ፤ የገነትንም ሰዎች ሰላም ለናንተ ይኹን በማለት ይጣራሉ፤ እነርሱም (የአዕራፍ ሰዎች) የሚከጅሉ ሲኾን ገና አልገቧትም›፡፡ (በአማርኛው ቁርአን 7.46 ላይ በጥቅሱ መካከል ለተጠቀሱት ሦስት ቁጥሮች የግርጌ ማስታዎሻ ማብራሪያ ተቀምጧል፡ ቁጥር 1. ‹በእሳትና በገነት መካከል› ቁጥር 2. ‹በገነትና በእሳት መካከል ያለ ኮረብታ ነው› ሲሉ ቁጥር 3. ደግሞ ‹ከሐዲዎች ፊታቸው በመጥቆር ምእመናኖች ፊታቸው በማብራት›) ይህ ሐሳብ የመጣው መክብብ 7.14 ላይ ከሚገኘውና በሚድራሽ ከተነገረው ላይ ነው፡፡ ‹በመንግስተ ሰማይና በሲዖል መካከል ምን ያህል ቦታ ነው ያለው?› ለሚለው ጥያቄ የተሰጠንም መረጃ በዚያ ይገኛል፡፡ ራባይ ዮሐናን መለሰ፡ግድግዳነው፡ ራባይ አካሃ አለ፡ስንዝርነው፡፡ ከዚያም ራባዮቹ አሉ ሁለቱም መንግስተ ሰማይና በሲዖል እርስ በእርስ ቅርብ ናቸው፣ ከዚያም የተነሳ የብርሃን ጨረር ከአንዱ ወደ ሌላኛው ያልፋል፡፡ ሐሳቡም ምናልባት የተወሰደው ከአቨስታ ሊሆን ይችላል፣ የዚህ በመንግስተ ሰማይና በሲዖል መካከል ያለው ልዩነት ሐሳብ ሚስዎንጋተስ በሚል ስያሜ በተጠቀሰበት (ፋርጋንድ 19)፡፡ እርሱምለበጎ ስራቸውና ለክፉ ስራቸው ለእያንዳንዱ እኩል 65 የሚመዝንላቸው ሰዎች ነፍሳት እንዲቀመጡበት የተወሰነ ቦታ ነው፡፡ በፓልቪ ደግሞ እርሱ ይጠራ የነበረው ሚስዎት-ጋስ ተብሎ ነበር፡፡ ዞሮአስተራውያን በሰማይና በሲዖል መካከል ያለው ርቀት በብርሃንና በጨለማ መካከል ያለው ርቀት እኩል ነው የሚልን ሐሳብ ነው የያዙት፡፡ የመልካም ስራቸው ከክፉ ስራዎቻቸው ጋር እኩል ለሆኑት ልዩ ቦታ ተጠብቆላቸዋል የሚለው ሐሳብ ወደ ሌሎች ሃይማኖቶችም ውስጥ ተላልፏል፡፡

ሰይጣን

በቁርአን 15.18 ላይ ሰይጣንን በተመለከተ እንደሚከተለው ተብሏል፡፡ እርሱና ሌሎች የወደቁ መላእክትወሬ መስማትን ለመስረቅእንደሚታገሉ ነው፡፡ ይህንንም የሚያደርጉት በሰማይ ላሉት መላእክት የሚሰጠውን የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት  ለመስማት ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ሐሳብ በቁርአን 37.8 ላይና 67.5 ላይ ተደግሟል፡፡ ይህ እምነት የመጣው ከአይሁዶች ነው፣ ምክንያቱም በሃጊጋ ውስጥ ምዕራፍ 6.1 የተነገረው ነገር ሰይጣናትከመጋረጃው በስተጀርባ ሆነው ይሰማሉይህም ስለሚመጡ የወደፊት ክስተቶች እውቀትን ለማግኘት ነው ይላል፡፡ ቁርአን ደግሞ ያቀረበው ተወርዋሪ ኮከቦች በመላእክት በኩል በእነሱ ላይ እንደሚወረወሩ ነው ይህም እነሱን ለማባረር እንደሆነ ነው፡፡

የፍርድ ቀን

በሱራ 50.30 ላይ የፍርድ ቀንን አስመልክቶ፣ እግዚአብሔር እንደሚከተለው እንደሚናገር ቀርቧልለገሃነም ሞላሽን?› የምንልበትንናጭማሪ አለን?› የምትልበትን ቀን (አስጠንቅቃቸው)› የሚለው ንግግር በኦትዮቱ ራባይ አኪባ 8 ቁጥር አንድ ላይ የምናነበው የገደል ማሚቶ ነው፡፡የሲዖል ልዑል አለ በቀን እና በቀን (ያም ቀን በቀን) ‹የሚታደስን ምግብ ስጠኝአለ፡፡ ይህ የአይሁድ ስራ  የኢሳያስን 5.14 ላይ የተነገረውን እውነታ ማስረጃ ያረጋግጣል፡፡

በቁርአን 11.40 እንደገና በቁርአን 23.27 ላይ የተነገረን ነገር በኖህ ጊዜእቶኑ በገነፈለ ጊዜየእንግሊዝኛው (በፈላ ጊዜ፡፡ ይህም ያለምንም ጥርጥር የሚያሳየው ወደ አይሁድ አመለካከት ነው (ሮሽ ሃሻና 16 ቁጥር 2 እና የሳንሄድሪን 108) ያምየጥፋት ውሃው ትውልድ በፈላ ውሃ ነው የተቀጡትየሚለውና የማያምኑት በኖህ ላይ አሾፉ የሚለው የቁርአን ጠቅላላ አረፍተ ነገሮች በሙሉ የተወሰዱት ከዚህ የሳንሄድሪን ትራክትና ከሌሎች የአይሁድ ተንታኞች ላይ ነው፡፡ ምናልባትም ይህንን ባለማወቅ ተንታኙ ጃላላይነ በቁርአን 11.40 ላይ የተናገረው እርሱየፈላው  የዳቦ ጋጋሪዎች መጋገሪያ ምድጃነበር፣ እርሱም የኖህ የጥፋት ጎርፍ ውሃ በደጅ እንደነበረ ምልክት ነበር ብሏል፡፡

የአይሁድ ልማድ በእስልምና ላይ ያደረሰውን እጅግ በጣም ከፍተኛ ተፅዕኖ በተመለከተ ሌላ ተጨማሪ ማስረጃ የሚፈለግ ከሆነ፣ ሊሆን የሚችለው በጣም አስገራሚ ያልሆኑ እውነታዎችን በመስጠት ይሆናል፡፡ ሙስሊሞች የቁርአንን አቀራረብና ንፁህ አረብኛነቱን እንደ ተዓምር ቆጥረው ከእግዚአብሔር የመጣ ማስረጃ ነው በማለት ጉራ ቢነፉበትም እንኳን፣ በውስጡ የሚገኙ አንዳንድ ቃላት ግን  ቁርአን ሙሉ ለሙሉ የአረብኛ ቋንቋ እንዳልሆነ ያሳያሉ፡፡ እነርሱም ከአርማይክ ወይንም ከዕብራይስጥ የተወሰዱ ናቸው፡፡ ከእነዚህም ውስጥ አንዳንዶቹ የተወሰዱት ለሁለቱም የጋራ ከሆኑ ቋንቋዎችም ሲሆን የተቀናበሩት ደግሞ በአረብኛ ቋንቋ የሰዋስው ሕግ መሠረት አይደለም፡፡ በአንፃሩ ከዕብራይስጥና ከአርማይክ ስለሆኑ ሰዋስዋዊ አቀናበራቸው ለእነዚህ ቋንቋዎች የሆኑ ናቸው፡፡ ፓራዳይዝ ወይንም ገነት የሚለው ቃል የተወሰደው ከኋለኛው ሒብሩ ቢሆንም፣ ነገር ግን ከጥንታዊው ፐርሺያ የመጣው ነው፡፡ ስለዚህም እርሱ የዚያ ቋንቋና የሳንስክሪት ቃል ነው፡፡ አንዳንድ ቃላት ለአንዳንድ ቋንቋዎች ባዕዶች እንደሆኑት ሁሉ፣ ይህም ቃል ለአረብኛ ቋንቋ ባዕድ ነው፡፡ የመሐመዳውያን ተንታኞች ለእንደዚህ ዓይነት ቃላት ትክክለኛ ትርጉም መስጠት ብዙውን ጊዜ ይከብዳቸዋል ምክንያቱም መሐመድ ከየትኛው ቋንቋ እንደተዋሳቸው አያውቁምና፡፡ በዚህ ዓይነት መንገድ ትርጉማቸውን ስናውቅ የምናገኘው ነገር ዓውዱን እንደሚገልጥ ነው፡፡ ለምሳሌም ያህል ማላኩት የሚለውን ቃል የመላእክትን ተፈጥሮ ወይንም መኖሪያ እንደሚገልጥ መገመት የተለመደ ስህተት ነው፣ ምክንያቱም ‹ማላክ›፣ ማለትም መልአክ ከሚለው ቃል አልመጣምና፡፡ ነገር ግን ማላኩት የሒብሩም ማልኩት ወይንም ‹መንግስት› የሚለውን ቃል በአረብኛ የማስቀመጪያ መንገድ ነውና፡፡ የአይሁድ የአምልኮ መልክ በመሐመዳውያን ላይ ያደረሰውም ተፅዕኖ አስገራሚነቱ በትንሹ የሚገመት አይደለም፡፡ መሐመዳውያውን በአምልኮ ልምምዳቸው ውስጥ እራሳቸውን መሸፈናቸው፣ በመስጊዶቻቸው ውስጥ ሴቶችና ወንዶችን ተለያይተው እንዲቀመጡ ማድረጋቸውን (ሴቶቹ በአደባባይ አምልኮ ፍፁም እንዳይካፈሉ ቢደረጉም)፡፡ እንዲሁም ጫማ ማውለቃቸውን ከአይሁዶች የተበደሩት መሆኑን መጠርጠር ስህተት ነው የሚሆነው፡፡ ምናልባትም እነዚህ ሁሉ የአረቦች እና የአካባቢው ሴማውያን ጎሳዎች ጥንታዊ ልማዶች ሊሆኑ ይችሉ ይሆናል፡፡ የሙስሊሞቹ የመንፃት ስርዓት በቀጥታ በአብዛኛው የተገለበጠው ከአይሁዶቹ ሊሆን ይችላል ምንም እንኳን መጠነኛ የጥርጥር በር ቢኖረውም፡፡ ወደ ኢየሩሳሌም አቅጣጫ መስገድ እንዳየነው ሁሉ ለጥቂት ጊዜያት በመሐመዳውያኑ ከአይሁዶች ተኮርጆ ነበር ነገር ግን በመጨረሻ መካ የቂብላ (የስግደት) አቅጣጫ ሆኖ ተወሰደ፡፡ የፆምን ወር ማክበር ከአይሁዶች ሳይሆን ከሳባውያን እንደተወሰደም አይተናል፡፡ ነገር ግን ከዚያ ፆም ጋር ተያይዘው ያሉት ሕጎች ያለምንም ጥርጥር አይሁዳዊ ናቸው፡፡ በቁርአን 2.187 ላይ በፆሙ ወራት ውስጥ ባሉት ሌሊቶች ሁሉ ድግስ መብላት በተፈቀደበት ቁርአን እንደሚከተለው ይናገራል፡ ‹ከጎህ የኾነው ነጩ ክርም ከጥቁሩ ክር (ከሌሊት ጨለማ) ለናንተ እስከሚገለጥላችሁ ድረስ ብሉ ጠጡም ከዚያም ፆምን እስከ ሌሊቲ ድረስ ሙሉ›፡፡ የክሮች ከለር መጠቀስ ትርጉም ሙስሊሞች ከፀሐይ መውጣት እስከ መጥለቅ እንዲፆሙ መታዘዛቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ በትክክል መፆም የሚጀመረው በቀኑ በስንት ሰዓት ነው? ለሚለው ጥያቄ ይህ ጥቅስ እንደሚለው በጉዳዩ ላይ ሕግን ማስቀመጥ አስፈላጊ ነበር፡፡ ሕጉም የተወሰደው በተመሳሳይ ጉዳይ ላይ በአይሁዶች ከተደነገገው ሕግ ላይ ነበር እርሱም ከሚሽና በረኮት (1ና ቁጥር 2) ‹ቀኑ የሚጀምረው አንድ ሰው ነጭን ክር ከጥቁር ለመለየት ከሚችልበት ቅፅበት ጀምሮ ነው› ከሚለው ላይ ነው፡፡

ፀሎት

ሙስሊሞች በሚገኙበት በማንኛውም አገር ውስጥ፣ የአምስቱ የፀሎት ሰዓቶች በሚመጡበት ጊዜ የሚመሩት የተነገረውን ፀሎት በዚያን ሰዓት ባሉበት ቦታ በቤት፣ በመስጊድ ውስጥ ወይንም በመንገድ ላይ ይሁኑ እንዲሉት ነው፡፡ ይህ ልምምድ አሁን ባለንበት ዘመን ውስጥ ለእነሱ ብቻ ልዩ የሆነ አድርገው ይመለከቱታል፡፡ ነገር ግን የእርሱ ጅማሬ ወይንም ምንጭ ምን እንደሆነ ብንጠይቅ አሁንም መመለስ ያለብን ወደ አይሁዶቹ ነው፡፡ በመሐመድ ጊዜ በአረቢያ ውስጥ ይኖሩ የነበሩትና መንፈሳዊዎች አይሁዶች በወንጌሎች ውስጥ ለባህላቸው ከፍተኛ ክብርን በመስጠት የእግዚአብሔርን ቃል ምንም እንዳልተጠቀሙበት የተገለፁት የፈሪሳውያኖቹ ዘሮች ናቸው፡፡ በጌታችን ጊዜ እነዚህ ፈሪሳውያን ‹በምኩራብና በመንገድ ዳር ላይ በመቆም በመፀለያቸው ተነቅፈው ነበር› ይህም ለነበራቸው መንፈሳዊ ትጋት ከሰዎች ዘንድ ከፍተኛ ዋጋን ለማግኘት በማለት ነበር፡፡ በጥንታውያኖቹ ፈሪሳውያንና በአሁኑ ጊዜ ሙስሊሞች ያለው መመሳሰል በጣም አስገራሚ ነው፡፡ ከሙስሊሞቹ መካከል አንዳንድ የክርስትና ጠላቶች የሚናገሩት ይሄ ወንጌል ለመበረዙ ማስረጃ እንደሆነ ነው፡፡ ምክንያቱም ከዚህ በላይ ጌታ ኢየሱስ ተናግሮታል ተብሎ የተጠቀሰው ጥቅስ የመሐመዳውያን አምልኮ ትክክለኛ መግለጫ ሲሆን ክርስትያኖች ሙስሊሞችንና የተሰጠ አምልኮአቸውን ካዩ በኋላ ለመኮነን የጻፉት ነው በማለት ይከራከራሉ፡፡ መሐመድና ተከታዮቹ አይሁዶችን በዚህ ጉዳይ ላይ እንደምሳሌ መውሰዳቸው ያልተለመደ ነገር አይደለም፡፡ እነርሱም አይሁዳውያኖቹ የአብርሃም ዘርና የመጽሐፉ ሰዎች እንደሆኑ ያውቃሉ፣ ስለዚህም አይሁዳውያን እንደሚያደርጉት በአምልኮ ውጫዊ ነገር ላይ ከፍተኛ ትኩረትን መስጠታቸው፣ የአይሁድ ዓይነት ክብር አሰጣጥን እውነተኛ ነው በማለት መውሰዳቸው አስደናቂ አይደለም፡፡ መሐመድ በእርግጥ ለተከታዮቹ የተናገረው፣ እንዴት ማምለክ እንዳለበት በመልአኩ ገብርኤል እንደተነገረው ነው፣ ስለሆነም እስከ አሁን ድረስ ሙስሊሞች እርሱን በመሰለ ሁኔታ ያጎነብሳሉ፡፡

የሚስቶች ቁጥር

እጅግ በጣም ግልጥ በሆነ መንገድ እስልምና ላይ ተፅዕኖ ካሳደሩት ከብዙዎቹ የአይሁድ ልማዶች አንዱን ብቻ እዚህ እንጠቅሳለን፡፡ በቁርአን 4.3 ላይ ‹በየቲሞችም (ማግባት) አለማስተካከላችሁን ብትፈሩ (ዝሙትንና ከተወሰነላችሁ በላይ ማግባትንም ፍሩ) ከሴቶች ለናንተ የተዋበላችሁን ሁለት ሁለት፣ ሦስት ሦስትም፣ አራት አራትም አግቡ፡፡ አለማስተካከልንም ብትፈሩ እንዲትን ወይም እጆቻችሁ ንብረት ያደረጉትን ያዙ፤ ይህ ወደ አለመበደል በጣም የቀረበ ነው፡፡› የእርሱ ተከታዮች በአንድ ጊዜ ውስጥ ሊኖራቸው ስለሚገባ የሚስቶች ቁጥርን ውሱን ማድረግን በተመለከተ ማለትም አራት ሚስቶችን ብቻ ስለማድረግ ለወደፊት የሚሆንን ሕግ መሐመድ አስቀምጧል፡፡ የሙስሊም ተንታኞች የሚነግሩን ከዚህ በፊት ብዙዎቹ (አረቦች) ከዚህ ቁጥር በላይ የሆኑ ሚስቶች እንደነበሯቸው ነው፡፡ ሕጉ ግን ለመሐመድ ለእራሱ አያገለግልም ምክንያቱም ከቁርአን 33.50 እንደምንማረው ከሆነ እርሱ የፈለገውን ቁጥር ያህል ሚስቶች እንዲያገባ ልዩ ፈቃድን ተሰጥቶት ነበርና፡፡ ቁጥርን የሚወስኑት ሕግጋት ቃሎች የሚል ሲሆን በተንታኞች ሁሉ ይህ ቃል ሲገለጥ የኖረው ሙስሊሞች በአንድ ጊዜ ከአራት በላይ ሚስቶችን እንደማያገቡ የተደነገገ መሆኑን ነው፡፡ መፍታትን በተመለከተ ግን ካገቧቸው ውስጥ አንዳቸውን ወይንም ሁሉን ለመፍታት ያልተወሰነ ነፃነት ሲኖራቸው የተሰጠውንም ቁጥር ለመሙላት ሌሎችን ማግባት እንደሚችሉ ነው፡፡

መሐመድ ይህንን ሕግ ከየት ነው የተዋሰው፣ እንዲሁም ለመሐመዳውያንም በአንድ ጊዜ አራት ሕጋዊ ሚስቶች ብቻ እንዲኖሯቸው ለምን መረጠ? ስንል አሁንም መልሱን የምናገኘው ይህንን በተመለከተ በተሰጠው በአይሁድ ሕግጋቶች ውስጥ ነው፡፡ እርሱም እንደሚከተለው ተጽፏል፡ ‹አንድ ሰው ብዙ ሚስቶችን ሊያገባ ይችላል ‹ራባይ› እንዳለው ይህንን ማድረግ ተፈቅዷል፣ ለእነርሱ እርሱ የሚያስፈልጋቸውን እስከሰጠ ድረስ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ብልህ ሰዎች አንድ ሰው ከአራት ሚስቶች በላይ እንዳያገባ የሚል መልካም ምክርን ሰጥተዋል›፡፡

ያልተማረው ነቢይ

በዚህ ምዕራፍና በሌሎችም ተከታዮች ውስጥ ላለው ሐሳብ፣ ቁርአን የመሐመድ ቅንብር ሳይሆን ከእግዚአብሔር የመጣ ነው ከሚለው አባባላቸው ባሻገር፤ መሐመዳውያን አንድ መልስ አላቸው፡፡ እነርሱም የሚግሩን መሐመድ ማንበብና መጻፍ አይችልም በማለት ነው፡፡ ስለዚህም እርሱ የዕብራይስጥን፣ የአርማይክን፣ እንዲሁም የቁርአንን መልእከት ያመጣባቸው ናቸው ያልናቸውን ሌሎችን ቋንቋዎችን ሊያጠና አይችልም ነበር ይላሉ፡፡ ይህም በቀጥታ ወይንም በተዘዋዋሪ በብዛት በቁርአን ውስጥ የሚገኙትን ሁሉ ይጨምራል፡፡ ስለዚህም ምንም ትምህርት ያልተማረው መሐመድ እንዲህ ዓይነት እጅግ በጣም ብዙ የሆኑ ጽሑፎችን በምንም መንገድ ሊመረምር አይችልም፣ አብዛኛዎቹም እርሱ በማያውቃቸው ቋንቋዎች ናቸው፣ እነርሱም አሁን ባሉት በጥቂቶች በስተቀር በማንም አይታወቁም› ይላሉ፡፡

ይህ ውይይት በሁለት ዋና ሐሳቦች ላይ የተመሰረተ ነው፣ አንደኛ መሐመድ አያነብም አይጽፍምም ነበር፣ እና ሁለተኛው ደግሞ በአይሁዶች፣ በክርስትያኖች፣ በዞሮአስተርያን እና በእርሱ ጊዜ በነበሩት ዘንድ ተቀባይነት የነበራቸውን ሌሌች ልማዶችና ተረቶችን በማንበብ ብቻ ነበር ሊማራቸው ይችል የነበረው የሚሉ ናቸው፡፡ ለእነዚህ ለሁለቱም የሚቀርቡት ማስረጃዎች በጣም ደካማዎች ናቸው፡፡ የቀደመውንም ለማረጋገጥ (እውነት ለማስመሰል) ቁርአን 7.157 ጋር ለማያያዝ ጥረት ተደርጓል፡፡ በዚያም ቦታ ላይ መሐመድ ‹አን-ናቢዩል ዑሚ› በአማርኛው ቁርአን ‹የማይጽፍና የማያነብ ነቢይ› ተብሎ ተሰይሟል፡፡ እነዚህንም ቃላት ሙስሊሞቹ የወሰዷቸው ‹ያልተማረው ነቢይ› በማለት ነው፡፡ ነገር ግን ራቢ አብራሃም ጊዩገር እንዳለው ‹አንሌተርድ› ወይንም ‹ያልተማረ› የሚለው ቃል በእውነት የሚለው ‹አሕዛብ› ማለት እንደሆነና አይሁድ ያልሆኑትን ሕዝብ እንደሚያሳይ ነው፡፡ ይህም የሚረጋገጠው በቁርአን 3.19 ነቢዩ እንዲናገር ከታዘዘው ጋር ‹ለዑሚንና ለመጽሐፉ ሰዎች› ብሎ ከተናገረው ላይ ነው፡፡ በዚህም ጥቅስ ውስጥ አረቦች በአጠቃላይ በዚህ ውስጥ በአህዛብ ውስጥ ተወክለዋል›፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በቁርአን 19.37 ውስጥ እንዲሁም 45.16፣ የነቢይነቱ ቦታ (ቢሮ) በግልጥ የተሰጠው ለይስሐቅ ቤተሰብ እና ለያዕቆብ እንደሆነ ተገልጧል እንጂ ለእስማኤል አይደለም፡፡ ስለዚህም መሐመድ እራሱን ያቀረበው እንደ አሕዛብ ነቢይ ነው›፡፡ በዚህም መሰረት መሐመድ እራሱን ከሌሎቹ በመለየት በአጠቃላይ አነጋገር ከይስሐቅ ዘር ከመጡት በመለየት አቅርቦበታል፡፡ ስለዚህም መሐመድ የማይጽፍና የማያነብ ለመሆኑ ምንም እርግጠኛ ማስረጃ በእውነት የለም፡፡ ሆኖም ግን  እርሱ በጥንቃቄ ጽፎታል የሚሉትን የቁርአንን ልዩ የሆነ የስነ ጽሑፍ ሁኔታ እንደማስረጃ መጥቀስ ከሚፈልጉት ጋር እራሳችንን ማስገባት አንፈልግም፡፡ ነገር ግን ያለ ጽሑፍ ችሎታ እንደተሰራ በማሰብ፤ የተለያዩ ቁርአኖችን ከማብራራት፤ በቃላቸው ከማጥናትና እነርሱንም ከመቅራት በፊት እርሱ ከሌሎች ምንጮች እንደገለበጣቸው ማወቅ አለባቸው፡፡

ነገር ግን ለመነጋገር ያህል እንኳን ማንበብና መጻፍ ለመሐመድ የማይታወቁ ክህሎቶች ናቸው ብለን ብንል፣ ይህንን ሐሳብ መቀበል በራሱ እርሱ ከአይሁዶች እና ከሌሎች ምንጮች እጅግ በጣም ብዙ የሆኑ ነገሮችን የተዋሰ መሆኑን ሊያፈርሰው አይችሉም፡፡ እርሱ አረብኛን ማንበብ ቢችልም እንኳን፣ የአርማይክ የዕብራይስጥና ሌሎች ቋንቋዎችን በጭራሽ የማያውቅ ሊሆን ይችላል፡፡ በቁርአን አንዳንድ አንቀፆችና በተለያዩ የአይሁድ ጽሑፎች መካከል ያስቀመጥናቸውና የሚገኙት ቅርብ የሆኑ መመሳሰሎች የቁርአን ምንጮች ምንድናቸው ለሚለው ጥሩ ማስረጃዎች ናቸው፡፡ ነገር ግን በማንኛውም አንድ ማስረጃ ላይ የቁርአን ጥቅሶች ከእንደዚህ ዓይነት ምንጮች ላይ በቀጥታ አልተተረጎሙም፡፡ በቁርአን ውስጥ ያሉት እጅግ በጣም ብዙዎቹ ስህተቶች መሐመድ ያገኘውን መልእክት የተቀበለው በቃል መሆኑን ያመለክታሉ፣ ምናልባትም እራሳቸው ብዙ የመጽሐፍት ትምህርት እውቀት ከሌላቸው ሰዎች ሳይሆንም አይቀርም፡፡ ይህ ነው ሁለተኛውን የሙስሊሞችን ግምት የሚከላከለው፡፡ ግልፅ ከሆኑ ብዙ ምክንያቶች የተነሳ መሐመድ እጅግ በጣም ብዙ የሆኑትን የአርማይክ፣ የዞሮአስተርያን እና የግሪክም መጽሐፍትን ለመመልከት አለመቻሉ ምንም ጥርጥር አልነበረውም፣ ነገር ግን ከአይሁዶች፣ ከፐርሺያኖች፣ እና ከክርስትያን ጓደኞቹና ከደቀመዛምርቶቻቸው በጊዜው የነበሩ ተረቶችን፣ ልማዶችንና አንዳንድ አፈታሪኮችን ለመማር በምንም ዓይነት መልኩ ቢሆን ችግር አልነበረበትም፡፡ ጠላቶቹም ቁርአንን ለማቀናበር እንዲህ ዓይነት ሰዎችን ተጠቅሟል በማለት ብዙ ጊዜ ይቃወሙት ነበር፣ ከቁርአን ከራሱ ላይና ከኢብን ሒሻም እምነት እንዲሁም ከሌሎች ተንታኞች እንደምንረዳው ሁሉ፡፡ የቁርአንን መጽሐፍ ቅንብር እረድተዋል ተብለው እንደዚህ ከተጠቀሱት ሌሎች መካከል፣ በቁርአን 46.9 ላይ የተጠቀሰው (የተነገረለት) አይሁዳዊ፣ በቁርአንና በአይሁድ ጽሑፎች መካከል ስላለው መስማማት እንደምስክር ሊጠቀስ ይችላል፡፡ የሙስሊም ተንታኞቹ አባሲ እና ጃላሌን ይህንን ክፍል በተመለከተ በሰጡት ማስታዎሻ የሚነግሩን ይህ ሰው አብዱላ ኢብን ሳላም ነበር በማለት ነው፤ ብናምን እርሱ ራውዳቱል አህባብ ነው፣ እርሱም ሙስሊም ከመሆኑ በፊት አይሁዳዊ ቄስ ወይንም ራባይ ነበር፡፡ በቁርአን 25.5እና 6 ላይ የመሐመድ ጠላቶች እንደሚከተለው እንዳሉ ተነግሮናል ‹ሌሎች በዚህ ነገር ረድተውታል› እንዲሁም እርሱ የተወሰኑትን ብቻ እንደጻፋቸውና ‹የጥንት ተረቶችን› በጠዋትና በማታው በግብረ አበሮቹ እንደተነገረው ተገልጧል፡፡ አባሲ እንደገለፀው የተጠቀሰው ሰው ጃብረ የክርስትያን ባሪያ፣ ያሳር (አቡ ፉካይሃ ተብሎ የሚታወቀው)፣ እንዲሁም አንድ ግሪካዊ አቡ ታከቢሃህ ነበሩ ይላል፡፡ በቁርአን 16.105 ላይ ደግሞ ‹በእርግጥ አንድ ሰው አስተምሮታል› ለሚለው ለክሱ መልስን ሲሰጥ መሐመድ ያቀረበው ብቁ ያልሆነን ሐሳብ ነው፡፡ እርሱም የተጠቀሰው ሰው ቋንቋ የባዕድ ነው በማለት ቁርአን እራሱ የተቀናበረው ግልፅ በሆነ አረብኛ ነው በማለት ነበር፡፡

ይህ መልስ ግልፅ የሆነውና የቀረበውን ክስ ለመመለስ ምንም ጥረትን አላደረገም፣ ማለትም ችግሩ አገልግሎት ላይ የዋለው ቋንቋ ሳይሆን በመሐመድ የተወሰዱትና በቁርአን ውስጥ የተነገሩት ታሪኮች ናቸው፡፡ አባሲ እንዳለው ቃየል የሚባል ክርስትያን እንደተጠቀሰ ነበር፣ የጃላሌን ትንተና አሁንም የጠቀሰው ግን ጃብር እና ያሳር ነበሩ በማለት ነው፡፡ ሌሎች ደግሞ የሚሰጡት አስተያየት ሳልማን፣ የመሐመድ በጣም ታዋቂው ደቀመዝሙርና ፐርሺያዊው ሰው ነበር፣ ሌሎች ደግሞ ሱሃይብ ነበር፣ ሌሎች አዳስ የሚባል መነኩሴ ነበር ይላሉ፡፡ እንዲሁም ደግሞ እኛ ‹ኡትማን እንዲሁም በተለይም ዋራካ የከዲጃ ማለትም የመሐመድ መጀመሪያ ሚስት የአጎት ልጆች፣ ከክርስትናና ከዘመኑ አይሁዳዊነት  ጋር ትውውቅ ነበራቸው፡፡ እነዚህም ሰዎች በመሐመድ የመጀመሪያ የነቢይነት ጊዜና ምናልባትም ቀደም ብሎም ባለው ሕይወቱ ላይ ቀላል የሆነ ተፅዕኖ እንዳላመጡ ነው፡፡ የጉዲፈቻ ልጁ ዛይድ ሶርያዊ ነበር፣ እንደ ኢብን ሒሻም (በኢብን ሒሻም መሠረት) እርሱ በመጀመሪያ ክርስትናን በግልፅ የተቀበለ እንደነበር ነው፡፡ መሐመድ ስለ ክርስትና አይሁድና ዞሮአስተርያን እምነት መረጃ ያገኘባቸው ከጓደኞቹ ውጪ የሆኑ ሌሎችም ሰዎች እንደነበሩ እንመለከታለን፡፡ ይሁን እንጂ ከእነዚህ ምንጮች የተወሰዱት አንቀፆች በሁኔታቸው በጣም ድብቅ (የተሳሳቱ ወይንም የተጭበረበሩ) ሆነው በመሐመድ ቀርበው ስለነበር፣ መሐመድ የጠየቃቸውና የነገሩትም ሰዎች እንኳን ማጭበርበሩን አላስተዋሉትም ነበር፡፡ ነገር ግን እነርሱ እነዚህ ነገሮች በመገለጥ የመጡ ናቸው ብለው አስበው ነበር፣ እንደተባሉትም ሁሉ ቢያንስ እስካሁን ድረስ የከበረውን የእግዚአብሔር ቃል ለማረጋገጥ የተገለጡ ናቸው በማለት ጓጉተውላቸው ነበር፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ መሐመድ ከእነዚህ ሰዎች የተቀበለውን መረጃ በቅልጥፍና ተጠቅሞ እነርሱን እራሳቸውን አታሎበታል፣ ሆኖም ግን ጠላቶቹን በዚህ ነገር ማታለል አልቻለም ነበር፡፡ ስለዚህም ጠላቶቹን ፀጥ ለማሰኘት በነበረው ጉጉት በመጨረሻው ላይ ወደ ሰይፍ መዘዛ ዞረ፡፡

በሚቀጥለው ምዕራፍ ውስጥ የምንተላለፈው ክርስትና፣ ጤናማው ማለትም እውነተኛው ወይንም ጤናማ ያልሆነው ማለትም የሐሰቱ በማደግ ላይ በነበረው እስልምና ልምምድና በቁርአን ቅንብር ላይ ያመጣውን ተፅዕኖ ወደ ማየት ነው፡፡

 

የአዘጋጁ ማሳሰቢያ፡-

በዚህ ሰፊ ታሪካዊ አሰሳ ውስጥ እጅግ በጣም ጠቃሚ ትምህርቶች ይገኙበታል፡፡ ከእነዚህም ጭብጥ ታሪካዊ ማስረጃዎች በመነሳት እንድ ሰው ሊደመድም የሚችለው የቁርአን ምንጩ መሠረት የሌላቸው አፈ ታሪኮችና ተረቶች መሆናቸውን ነው፡፡ ሆኖም ተረቶቹ ከእግዚአብሔር የመጡ ናቸው ተብለው በረቀቀ መንገድ ስለቀረቡ ብዙ ሰዎች ለዘመናት ተሳስተውባቸዋል፣ አሁንም ብዙዎች እንደተሳሳቱባቸው ነው፡፡

መሐመድ ከልዩ ልዩ ምንጮች የሰበሰባቸውን ተረቶች ይቆጥራቸው የነበረው ከእርሱ በፊት ለነበሩት ነቢያት የተሰጡ ናቸው በማለት እንደነበረ ጥርጥር የለውም፡፡ መሠረቱ ሲፈተሸ ግን ምንጮቹ ሁሉ ተረቶችና ከእግዚአብሔር ቃል ጋር የማይሄዱ የእግዚአብሔርን ቃል ደረጃ የማይመጥኑ ናቸው፡፡

የዚህ ገፅ አዘጋጆች ዋና ዓላማ ሙስሊሞች ይህንን ታሪካዊ ሐቅ ተገንዝበው እንከን ወደሌለበት፣ በራሱ በእግዚአብሔር በተገለጠ የእግዚአብሔር እምነት እንዲመጡ ነው፡፡ በእግዚአብሔር ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰው ሕይወት ባሕሪይ በጣም ግልፅ ሆኖ ተቀምጧል፡፡ ሰው በተፈጥሮው ኃጢአተኛ በመሆኑ ከፈጠረው ቅዱሱ እግዚአብሔር በጣም የራቀ ነው፡፡ እውነተኛው እግዚአብሔር ቅዱስና ንፁህ ነው፣ ኃጢአተኛውን ይቅር ለማለትና ለመቀበል መንገድን ያዘጋጀው እራሱ ነው፣ መንገዱም ከቅዱስነቱና ከንፁህነቱ ጋር በፍፁም አይቃረንም፤ ነገሩን በጥሞና ለሚያስብ ሰው ሁሉ ሎጂካል ነው፡፡

እናንተ በእውነት ከእግዚአብሔር ጋር መታረቅ እንዳለባችሁ ተገንዝባችሁ ከሆነ መንገዱ አንድ ብቻ ነው፡፡ እርሱም ለኃጢአት ፍርድ ዋጋ በከፈለው በክርስቶስ ኢየሱስ በኩል ብቻ መምጣት ነው፡፡ እርሱ በክርስቶስ በኩል ንስሐ በመግባት ወደ እርሱ የሚመጣውን ለመቀበል እና አዲስንም ሕይወት ለመስጠት ቃል ገብቷል፡፡ እግዚአብሔር ይህንን አስደናቂና የማይለወጥ እውነት እንዲገልጥላችሁ፤ በራሱም መንገድ ወደ እራሱ እንዲያመጣችሁ የዘወትር ፀሎታችን ነው፡፡

 

የትርጉም ምንጭ: THE ORIGINAL SOURCES OF THE QUR'AN 

ሙሉ መጽሐፉ በአማርኛ:  የቁርአን የመጀመሪያ ምንጮች

ለእስልምና መልስ አማርኛ  ዋናው ገጽ